የሀገር ውስጥ ዜና

ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ተጋላጭነትን ለመቀነስ የሚረዳ ፕሮጀክት ይፋ ሆነ

By Amele Demsew

February 06, 2024

አዲስ አበባ፣ ጥር 28፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢትዮጵያ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ተጋላጭነትን ለመቀነስ የሚረዳ ፕሮጀክት ይፋ ተደርጓል።

ፕሮጀክቱ “ኢኔብል” የተሰኘ ሲሆን ፥ የኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ከኖርዌይ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ጋር በመተባበር የሚተገብሩት መሆኑ ተጠቆሟል፡፡

4ሚሊየን ዶላር በጄት የተያዘለት ይህ ፕሮጀክት ለሚቀጥሉት አራት ዓመታት የሚተገበር መሆኑ ተመላክቷል፡፡

”ኢኔብል” ፕሮጀክት በተለይ ነፍሰጡር እናቶችና ጽንሳቸው በአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖ ሥር እንዳይወድቅ ማድረግ እንዲሁም በምግብ እጥረትና በሌሎች ምክንያቶች ለተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች እንዳይጋለጡ የሚያስችል ፕሮጀክት ነው ተብሏ

በፕሮጀክቱ በአዲስ አበባ፣ በአዳማ፣ በሐረርና በጅማ ከተሞች ባሉ የጤና አገልግሎት መስጫ ተቋማት ላይ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ተጋላጭነትን ለመቀነስ የሚያግዙ ሥራዎች እንደሚከናወኑም ነው የተገለጸው።

የኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ጌታቸው ቶሌራ(ዶ/ር) እንዳሉት ÷ ፕሮጀክቱ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ሥርጭትንና ተጋላጭነትን ለመቀነስ በተለይ በነፍሰጡር እናቶችና በህፃናት ላይ ትኩረት አድርጎ ይሰራል፡፡

ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች የዜጎችን ምርታማነት የሚገድብ መሆኑን ገልጸው ÷ ፕሮጀክቱ ሥር የሰደዱ ተላላፊ በሽታዎች ቅነሳ እንዲሁም ምርታማነት እንዲያድግ በማድረግ በኩል አዎንታዊ ሚና እንደሚኖረው አስረድተዋል።

የ”ኢኔብል” ፕሮጀክት አስተባባሪ ዶ/ር ኢሌኒ ፓፓዶፓሉ በበኩላቸው ÷ ፕሮጀክቱ በሚተገበርባቸው የጤና ተቋማት ውስጥ ለነፍሰጡር እናቶች ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች መከላከልና ክትትል እንደሚደረግ መግለጻቸውን የዘገበው ኢዜአ ነው፡፡