የሀገር ውስጥ ዜና

በፕሪቶሪያው ስምምነት የፌደራል መንግስትና የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር በርካታ ድሎችን አስመዝግበዋል – ጠ/ሚ ዐቢይ (ዶ/ር)

By Feven Bishaw

February 06, 2024

 

አዲስ አበባ፣ ጥር 28፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በፕሪቶሪያው ስምምነት የፌደራል መንግስትና የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር በትብብር በርካታ ድሎችን አስመዝግበዋል ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ተናገሩ፡፡

6ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 3ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 14ኛ መደበኛ ስብሰባ እየተካሄደ ሲሆን÷ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከምክር ቤት አባላት ለተነሳላቸው የተለያዩ ጥቄዎች ምላሽ እና ማብራሪያ እየሰጡ ነው፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) በማብራሪያቸው÷ በአማራ ክልልም ሆነ በኦሮሚያ ክልል የሰላም ጥሪ በተደጋጋሚ መቅረቡን አንስተዋል፡፡

በዚህም ሽብርተኛው ሸኔም ሆነ በአማራ ክልል የሚንቀሳቀሱ ፅንፈኛ ኃይሎች በሰላም ውይይት መሳሪያቸውን አስቀምጠው ሰላማዊ የፖለቲካ ትግል ማድረግ እንዲችሉ የፌደራል መንግስትም ሆነ የክልል መንግስት ዝግጁ መሆናቸውን በድጋሚ አረጋግጣለሁ ብለዋል፡፡

“እኛ የምንፈልገው ሰላም ነው፤ እኛ የምንፈልገው በሰላማዊ መንገድ ሀገራችንን ወደ ሚቀጥለው ደረጃ ማሸጋገር ነው” ብለዋል፡፡

ከግጭት ከፀብ የምናተርፈው ነገር የለም በማለት ገልጸው፤ በሰላም ነገሮችን ማየት እና መፍታት እንደሚገባም ተናግረዋል፡፡

ግጭት አጎደለ እንጂ የጨመረው ነገር የለም፤ ከመጉደል ውጭ ግጭት ትርፍ የለውም ብለዋል፡፡

ለዚህም የሀይማት አባቶች፣ ወጣቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች እና ምሁራን የሚጠበቅባቸውን ሚና እንዲጫወቱ ጥሪ አቅርበው የፌደራል መንግስትም ለሰላም ዝግጁ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

ህዝቡም የሚደገፍበትን ነገር ቢያውቅ ጥሩ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ መንተራስ ያለብን ደገፍ የሚያደርገንን ነገር ነው፤ የማያዘልቀንን ነገር ተደግፈን ወደ ጥፋት ከምናመራ በተቻለ መጠን ሰላማዊ ውይይት ብንከተል መልካም ነው ብለዋል፡፡

የፕሪቶሪያው ስምምነት አፈጻጸምን በተመለከተ በሰጡት ማብራሪያ÷ በፕሪቶሪያው ድርድር ከተደረገ በኋላ መንግስት በይፋ ለህዝብ መግለጹን፤ የአፍሪካ ህብረትም አደራዳሪ ስለነበር ለመላው ዓለም ስምምነቱን ማሳወቁንና የተደበቀ ነገር እንደሌለ አውስተዋል።

ከንግግሩ በኋል ምን ተገኘ ለሚለው ደግሞ የፌደራል መንግስትና የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር በትብብር በርካታ ድሎችን አስመዝግበዋል ነው ያሉት፡፡

በዚህም አውሮፕላን ማሪፊያዎችን በመጠገን የአየር ትራንስፖርት ማስጀመር ተችሏል፤ በ100 ሚሊየኖች የሚቆጠር ብር በማውጣት የቴሌኮም አገልግሎት እንዲጀመር ተደርጓል፡፡

የመብራት አገልግሎትም ተጠግኖ አገልግሎት እንዲሰጥ ተደርጓል፤ ብሄራዊ ባንክ 10 ቢሊየን ጥሬ ብር በመስጠት በክልሉ የባንክ አገልግሎት አስጀምሯል ብለዋል፡፡

በተጨማሪም ከስምምነቱ በኋላ 217 ፋብሪካዎች ስራ ጀምረዋል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ የትምህርትና የጤና ተቋማትም አገልግሎት እየሰጡ ነው ብለዋል፡፡

በክልሉ ባለፈው ክረምት 630 ሺህ ሄክታር መሬት መታረሱንም በማብራሪያቸው ጠቁመው፤ ይህ ትልቅ እምርታ ነው፤ ነገር ግን በቀጣይም ቀሪ ስራዎች አሉ እነርሱን በትብብርና በውይይት መስራት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን በተመለከተም÷ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በቁጥጥር ስር ከዋሉ ተጠርጣሪዎች መካከል አብዛኛዎቹ ትምህርት ተሰጥቷቸውና ሰልጥነው መለቀቃቸውን ገልፀዋል፡፡

ነገር ግን በሂደቱ የሚፈጠሩ ስህተቶች እንዳይኖሩ የአዋጁ መርማሪ ቦርድ እየሰራ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ይህን አልፎ የሚከሰት ስህተት ካለም የማስተካከል ስራ የሚከናወን ይሆናል ብለዋል፡፡

የአዋጁ ዋነኛ ዓላማም የሀገር ሰላምና ህልውናን መጠበቅ መሆኑን አንስተዋል፡፡