አዲስ አበባ፣ ጥር 27፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን የእስራኤል-ሃማስ ጦርነት ከተጀመረ ወዲህ ለአምስተኛ ጊዜ ወደ መካከለኛው ምስራቅ አቅንተዋል።
ጉብኝቱ አሜሪካ የየመን ሁቲ አማፂያን የሚያደርሱትን የሚሳኤል ጥቃት ለማስቆም ተጨማሪ እርምጃ መውሰዷን ትናንት ይፋ ማድረጓን ተከትሎ የተወሰነ ነው ተብሏል፡፡
ጦሩ በቀይ ባሕር የሚተላለፉ መርከቦችን ለመምታት የተዘጋጁ የምድር ላይ ጥቃት አድራሽ ክሩዝ ሚሳኤል እና አራት ፀረ-መርከብ ሚሳኤሎችን መደብደቡ ተናግሯል።
አሜሪካ እና እንግሊዝ በጋራ በቀይ ባሕር ዓለም አቀፍ መርከቦች መተላለፊያ ላይ በሁቲዎች የሚደርሰውን ጥቃት ለማስቆም በማሰብ የተጀመረው ጥቃትም መጠኑ እያደገ መምጣቱ ተገልጿል፡፡
የጋራ ጥቃቱ በኢራን ይደገፋል የተባለው ቡድን በቀይ ባሕር ከእስራኤል ጋር ግንኙነት አላቸው ባላቸው ወታደራዊ እና የንግድ መርከቦች ላይ ያደረሰውን ጥቃት ተከትሎ የተሰነዘረ መሆኑ ተጠቅሷል።
አሜሪካ ከሳምንት በፊት በዮርዳኖስ በሰው አልባ አውሮፕላኖች ለተፈፀመው ጥቃት ምላሽ ለመስጠት ከኢራን ጋር ግንኙነት አላቸው በተባሉ ኢላማዎች ላይ ተጨማሪ ጥቃት ለማድረስ ዕቅድ ማውጣቷን አስታውቃለች፡፡
ምንም እንኳን ኢራን የተሰነዘረባት ውንጀላ መሰረተ ቢስ ነው ብትልም÷ በኢራን እንደሚደገፍ የሚነገርለት በኢራቅ የሚገኘው ታጣቂ ቡድን ግን ሃላፊነቱን እንደወሰደ ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
በጋዛ ውስጥ የሚገኙ ከ100 የሚልቁ ታጋቾች እንዲፈቱ እና በግዛቱ ውስጥ ላሉ ንጹሃን አስፈላጊው ሰብዓዊ እርዳታ ለማድረስ ጦርነቱ በሚቆምበት ሁኔታ ላይ ከስምምነት ለመድረስ የሚለው ዋነኛ አጀንዳቸው እንደሚሆንም ተጠቁሟል፡፡
ብሊንከን አሜሪካ በቀጣናው የተከሰተው ውጥረት እንዲረግብ ሳይሆን እንዲባባስ እያደረገች ነው የሚል አመለካከት ካላቸው ወገኖች ትልቅ ፈተና ሊገጥማቸው እንደሚችልም በዘገባው ተመላክቷል፡፡