አዲስ አበባ፣ ጥር 27፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በሙሉ አቅሙ ወደ ሥራ ሲገባ ለ20 ሺህ ወገኖች የሥራ ዕድል የሚፈጥረው ለሚ ናሽናል ሲሚንቶ ፋብሪካ በቅርቡ ወደ ምርት እንደሚገባ ተገለጸ፡፡
የአማራ ክልል እና የዞን ከፍተኛ አመራሮች የለሚ ናሽናል ስሚንቶ ፋብሪካን ጎብኝተዋል፡፡
የፋብሪካው ምክትል ሥራ አሥኪያጅ አበባው በቀለ በዚሁ ወቅት እንዳሉት÷ ፋብሪካው ግንባታው ተጠናቆ በቅርቡ ወደ ምርት እንደሚገበ አረጋግጠዋል፡፡
በሙሉ አቅሙ ወደ ሥራ ሲገባም በቀን ከ130 ሺህ እስከ 150 ሺህ ኩንታል ሲሚንቶ ያመርታል ማለታቸውን አሚኮ ዘግቧል፡፡
የአማራ ክልል የከተማ እና መሰረተ ልማት ቢሮ ኃላፊ አህመዲን መሐመድ (ዶ/ር) በበኩላቸው÷ ለሚ ሲሚንቶ ፋብሪካ በጥሩ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ተመልክተናል ብለዋል፡፡
ለግንባታው ዘርፍ ተግዳሮት የሆነውን የስሚንቶ እጥረት እንደሚቀርፍምያላቸውን እምነት ገልጸዋል፡፡