የሀገር ውስጥ ዜና

የባሕር ዳር አባይ ወንዝ ድልድይ መዳረሻ መንገድ የአስፓልት ንጣፍ ሥራ ተጀመረ

By Amele Demsew

February 05, 2024

አዲስ አበባ፣ ጥር 27፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በባሕር ዳር ከተማ በመጠናቀቅ ላይ የሚገኘው የአባይ ወንዝ ድልድይ መዳረሻ መንገድ ግንባታ ፕሮጀክት የአስፓልት ንጣፍ ሥራ መጀመሩን የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር ገለጸ፡፡

ከሄኒ ጋርደን አደባባይ እስከ ዘንዘልማ መገንጠያ የሚዘልቀው 4 ነጥብ 7 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው የባሕር ዳር አባይ ወንዝ ድልድይ መዳረሻ መንገድ የአፈር ቆረጣና ሙሌት እንዲሁም የመፋሰሻ ቱቦ ዋና ዋና ሥራ በአብዛኛው መጠናቀቁ ተገልጿል፡፡

በተጨማሪም የሰብቤዝ ንጣፍ ፣ የቤስ ኮርስ ንጣፍ ፣ የቤዛዊት መንገድ መሿለኪያ እና መወጣጫዎች ሙሌት እንዲሁም የከርብስቶን ስራዎች ሲከናወን ቆይቶ ወደ አስፓልት ንጣፍ ሥራ መሸጋገሩ ተጠቁሟል፡፡

የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክቱ የአፈፃፀም ደረጃ 38 ነጥብ 2 በመቶ መድረሱን የአሥተዳደሩ መረጃ አመላክቷል፡፡

የአስፋልት እና የትራፊክ ምልክት ተከላ፣ የቀለም ቅብ ሥራ፣ የመንገድ መብራቶች ተከላ እና የእግረኛ መንገድ ንጣፍ ሥራ ለመጀመር ዝግጅት እየተደረገ መሆኑም ተጠቅሷል፡፡

መንገዱ የእግረኛ እና አካፋይን ጨምሮ መደበኛ ቦታዎች ላይ 51 ሜትር እንዲሁም የሕዝብ ማጓጓዣ ማቆሚያ ቦታዎች ላይ 59 ሜትር ስፋት አለው ተብሏል፡፡

እንዲሁም በአንድ ጊዜ በግራ እና ቀኝ 6 መኪናዎችን ማስተናገድ እንዲችል ተደርጎ እየተገነባ መሆኑ ተመላክቷል፡፡

የመንገዱ ግንባታ የሚከናወነው ከ825 ሚሊየን 659 ሺህ ብር በላይ በሆነ ወጪ መሆኑም ነው የተገለጸው፡፡