የሀገር ውስጥ ዜና

ለሰላም ጉዳይ ፍቱን የሆኑ ሀሳቦችን ማንሳት፣ መወያየትና የየድርሻችንንም መውሰድ አስፈላጊ ነው – አቶ ፍቃዱ ተሰማ

By Meseret Awoke

February 04, 2024

አዲስ አበባ፣ ጥር 26፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ለሰላም ጉዳይ ፍቱን የሆኑ ሀሳቦችን ማንሳት፣ መወያየትና የየድርሻችንንም መውሰድ አስፈላጊ ነው ሲሉ የብልፅግና ፓርቲ የኦሮሚያ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ኃላፊና የብልፅግና ፓርቲ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል ፍቃዱ ተሰማ ገለጹ፡፡

በደብረ ብርሃን ከተማ የተካሄደው ውይይት ህዝብ የሚያነሳቸውን ጥያቄዎች በውይይት ለመፍታት ምቹ ሁኔታዎችን መፍጠርና የአማራ ክልል በሙሉ አቅሙ ወደ ልማት መግባት እንዲችል ዓላማ ያደረገ እንደሆነ ተገልጿል።

ውይይቱን የመሩት የብልፅግና ፓርቲ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባላት ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር ኢ/ር )፣ የብልፅግና ፓርቲ የኦሮሚያ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ኃላፊና የብልፅግና ፓርቲ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል ፍቃዱ ተሰማ እና የብልፅግና ፓርቲ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል አህመዲን መሀመድ (ዶ/ር) ናቸው፡፡

ከደብረ ብርሃን ከተማ አስተዳደርና ከሰሜን ሸዋ ዞን የተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች የተውጣጡ ተሳታፊዎች ከህዝብ የሚነሱ ጥያቄዎችን በወቅቱ መፍታት እንደሚገባም አሳስበዋል።

የክልሉን ሰላም ወደነበረበት ለመመለስ ሰፊ ውይይቶች መደረግ እንዳለባቸው ያሳሰቡት ተሳታፊዎቹ፥ ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታትም ትኩረት እንዲደረግ መጠየቃቸውን ከብልጽግና ፓርቲ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

የብልፅግና ፓርቲ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር ኢ/ር) በበኩላቸው እንዳሉት፥ በአማራ ክልል በተፈጠረው የፀጥታ ችግር ማህበረሰቡን በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ላይ ተፅዕኖ ያሳደረና ለማህበራዊ አለመረጋጋትም የዳረገ ነው።

ለሰላም ጉዳይ ፍቱን የሆኑ ሀሳቦችን ማንሳት፣ መወያየትና የየድርሻችንንም መውሰድ አስፈላጊ ነው ያሉት ደግሞ በብልፅግና ፓርቲ የኦሮሚያ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ሀላፊና የብልፅግና ፓርቲ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል ፍቃዱ ተሰማ ናቸው።

አህመዲን መሀመድ (ዶ/ር) በበኩላቸው፥ የክልሉን ሰላም ወደ ዘላቂና አስተማማኝ ደረጃ ለማድረስ በመንግስት በኩል ለሚወሰዱ የመፍትሄ አማራጮች አጋር መሆንና ሰላምን ለማስጠበቅ ማህበረሰቡ የድርሻውን እንዲወጣ ጠይቀዋል።

#Ethiopia

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision ኢንስታግራም፦ https://www.instagram.com/fana_television/ ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!