የሀገር ውስጥ ዜና

አቶ ሽመልስ ቱሪዝሙን ለማነቃቃት የተጀመረው ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገለጹ

By Shambel Mihret

February 03, 2024

አዲስ አበባ፣ ጥር 25፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ቱሪዝሙን ለማነቃቃት የተጀመሩ ሥራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መሥተዳድር ሽመልስ አብዲሳ ገለጹ፡፡

ርዕሰ መሥተዳድር ሽመልስ በቢሾፍቱ ከተማ በ750 ሚሊየን ብር ወጪ የተገነባውን ባለ አምስት ወለል “ኖራ ሪዞርት” መርቀው ሥራ አስጀምረዋል፡፡

በምረቃ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ ባደረጉት ንግግርም ቱሪዝሙን ለማነቃቃት የተጀመሩ ሥራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ጠቅሰው÷ ዛሬው የተመረቀው ሪዞርትም የዚሁ ማሳያ ነው ብለዋል፡፡

እንደሀገር ከፍተኛ ትኩረት የተሰጠው የቱሪዝም ዘርፍ ስኬታማ እንዲሆን የክልሉ መንግሥት እምቅ አቅሞቹን ለይቶ ባለሀብቶችን በማሳተፍና በየደረጃው ያሉ አመራሮችን በማሰማራት እየሠራ ነው ብለዋል።

ከተሞቻችን የቱሪዝም ማዕከላት እንዲሆኑ እየተሠራ ነው ያሉት አቶ ሽመልስ÷ በምቹ አቀማመጥ እንዲሁም ሰፊ የኢንቨስትመንት አማራጮችን በመያዝ ቢሾፍቱ ግንባር ቀደም መሆኗን ጠቅሰዋል፡፡

በከተማዋ የሆቴልና የሪዞርት አገልግሎት ፍላጎት በከፍተኛ ደረጃ መጨመሩን ጠቁመው÷ አሁንም በዘርፉ መሰማራት የሚፈልጉ ባለሀብቶች ኢንቨስት እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ዛሬ የተመረቀው ሪዞርት በ5 ሺህ ካሬ ሜትር ላይ ያረፈ ሲሆን ለ250 ዜጎችም የሥራ ዕድል መፍጠሩ ተገልጿል፡፡