አዲስ አበባ፣ ጥር 25፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ በአፋር ክልል ሠመራ ከተማ ለሚያስገነባው የወንጀል ምርመራ ቢሮ የመሠረት ድንጋይ ተቀመጠ፡፡
የመሰረት ድንጋዩን ያስቀመጡት÷ የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገ/ሚካኤል እና የሠመራ ከተማ ከንቲባ አብዱ ሙሳ ናቸው፡፡
ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገ/ሚካኤል በዚሁ ወቅት ባደረጉት ንግግር÷ በሠመራ የወንጀል ምርመራ ማዕከል ለመገንባት 10 ሺህ ካሬ ሜትር የመሬት ርክክብ መደረጉን እና ዲዛይን መዘጋጀቱን አስታውቀዋል፡፡
በክልሉ ለሚሠሩ የፖሊስ አመራሮችና አባላት የመኖሪያ ቤት እንዲመቻች እና ለወንጀል መከላከልና ምርመራ የሚያግዙ ዘመናዊ የስልጠና ማዕከላትን ያካተተ ግንባታ እንደሚከናወንም ጠቅሰዋል፡፡
የክልሉ አመራሮችም ለመሬት አቅርቦቱ ድጋፍ እንዳደረጉት ሁሉ ለግንባታው መጠናቀቅም እንዲተባባሩ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
የፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ምክትል ኮሚሽነር ጀነራል ዘላለም መንግስቴ÷ ተቋሙ ወንጀሎችን በመከላከልና መርምሮ ለሕግ የማቅረብ፣ ከፀጥታ አካላት ጋር በመሆን የታቀዱ ወንጀሎችን የመቆጣጠር ስራዎች ስኬታማ በሆነ መልኩ እያከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።
የሠመራ ከተማ ከንቲባ አብዱ ሙሳ በበኩላቸው÷ ፕሮጀክቱ የክልሉን ዕድገት የሚያፋጥን ከመሆኑም ባሻገር ለማኅበረሰቡ የሥራ ዕድል የሚፈጠር በመሆኑ ድጋፋችንን እንቀጥላለን ማለታቸውን የፌደራል ፖሊስ መረጃ ያመላክታል፡፡