የሀገር ውስጥ ዜና

የኢትዮ ኢንጅነሪንግ ግሩፕ የጥራት ስራ አመራር ስርዓት ትግበራ እውቅና አገኘ

By Amele Demsew

February 02, 2024

አዲስ አበባ፣ ጥር 24፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮ ኢንጅነሪንግ ግሩፕ እና በስሩ የሚገኘው አዲስ ማሽንና መለዋወጫ ማምረቻ ኢንዱስትሪ የጥራት ስራ አመራር ስርዓት (ISO) ትግበራ እውቅና አገኙ::

ግሩፑ ከለውጡ በፊት በነበረው አደረጃጀት እና ተልዕኮ የምርትና አገልግሎት ጥራት ችግር እንደነበረበትና የደምበኛን ፍላጎት ያልጠበቁ ምርቶች የሚመረቱበት የልማት ድርጅት እንደነበር ተገልጿል::

ለውጡን ተከትሎ ተቋሙ የአሰራርና የአደረጃጀት ለውጥ በማምጣቱ ጥራታቸውን የጠበቁ ምርቶችን ማምረት መጀመሩን የግሩፑ ዋና ስራ አስፈፃሚ አምባሳደር ሱሌማን ደደፎ ገልፀዋል::

በዚህም ተቋሙ ሀገርን የሚጠቅም ተቋም እንዲሆን በርካታ ስራዎች መሰራታቸውን አስረድተዋል።

በጥራት የተለያዩ ምርቶችን በማምረትም በሀገር ውስጥ የሚታየውን የምርት ክፍተት ለመሙላትም ተቋሙ እየሰራ ነው ብለዋል::

ሌሎችም በስሩ የሚገኙ እንዱስትሪዎች በጥራት እውቅና እንዲያገኙ እንደሚሰራም ተናግረዋል::

የኢትዮጵያ ተስማሚነት ምዘና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር መዓዛ አበራ በበኩላቸው÷ ተቋሙ በአለም አቀፍ የምርት ጥራት አሰራር ለመስራት ያሳየው ቁርጠኝነት የሚደነቅ ነው ብለዋል::

በዘቢብ ተክላይ