Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

የአውሮፓ ህብረት ለዩክሬን የ54 ቢሊየን ዶላር ድጋፍ አጸደቀ

አዲስ አበባ፣ ጥር 24፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የአውሮፓ ህብረት ለዩክሬን ተጨማሪ የ54 ቢሊየን ዶላር ድጋፍ ይፋ አድርጓል፡፡

ድጋፉን የ27ቱም የህብረቱ አባል ሀገራት መሪዎች በሙሉ ድምጽ ያጸደቁት መሆኑ ነው የተገለጸው፡፡

የተደረገው ድጋፍ የዩክሬን ኢኮኖሚ በሁሉም ዘርፍ የተረጋጋ ሆኖ እንዲቀጥል ለማስቻል ያለመ መሆኑን የህብረቱ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ቻርለስ ሚሼል ተናግረዋል፡፡

በተለይም ጤና ተቋማትን፣ ማህበራዊ ዋስትናን፣ ጡረታን እና ሌሎች የአገልግሎት ዘርፎችን ለማጠናከር እንደሚውል ተመላክቷል፡፡

ከዚህ ባለፈም ዩክሬን ከሩሲያ ጋር እደረገች ላለው ጦርነት ሁለንተናዊ አቅሟን ለማጎልበት እንደሚያስችላት መጠቆሙን ሲኤንቢሲ ዘግቧል፡፡

የዩክሬን ፕሬዚዳንት ቮሎድሚር ዘሌንስኪ÷ የአውሮፓ የህብረት አባል ሀገራት ድጋፉን በሙሉ ድምጽ ማጽደቃቸው የህብረቱን አንድነት የሚያረጋግጥ ነው ብለዋል፡፡

ለተደረገው አዲስ ድጋፍ ያመሰገኑት ፕሬዚዳንቱ÷ ህብረቱ በቀጣይ የሚያደረገውን ድጋፍ እንዲያጠናክርም ጠይቀዋል፡፡

Exit mobile version