የሀገር ውስጥ ዜና

የሥራና ክህሎት ሚኒስቴርና እናት ባንክ በጋራ ለመስራት ተስማሙ

By Amele Demsew

February 01, 2024

አዲስ አበባ፣ ጥር 23፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የሥራና ክህሎት ሚኒስቴርና እናት ባንክ በጋራ መስራት የሚያስችላቸውን የመግባቢያ ስምምነት ዛሬ ተፈራርመዋል፡፡

ስምምነቱ በዋናነት ሴቶችን ያማከለ የሀገር ውስጥ የስራ ዕድል ፈጠራ፣ የፈጠራ ሃሳብ ውድድሮችን መደገፍ እና የፋይናንስ ድጋፍ አቅርቦት ላይ ትኩረት እንደሚያደርግ ተመላክቷል፡፡

በተጨማሪም አካታች የስራ ዕድል ፈጠራ እና የፋይናንስ አቅርቦትና ተደራሽነትን በማሻሻል ረገድ ጉልህ ሚና ይኖረዋል ተብሏል፡፡

ከስምምነቱ ጎን ለጎን የፈጠራ ሃሳብ ያላቸው ሴቶች ብቻ የሚሳተፉበት “የብሩህ እናት 2016” ውድድር ማስጀመሪያ ስነ ስርዓት ተካሂዷል።

ይህ ውድድር ባለፉት ሦስት ዓመታት በሀገር ዓቀፍ ደረጃ ሃሳብ ያላቸውን ወጣቶች በማወዳደር እውቅና፣ ስልጠና እና የፋይናንስ ድጋፎችን ሲያቀርብ የቆየው “የብሩህ ኢትዮጵያ” የስራ ፈጠራ ሃሳብ ውድድር አካል መሆኑ ተጠቁሟል።

ስምምነቱንም የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ዴኤታ ንጉሱ ጥላሁን እና የእናት ባንክ ምክትል ፕሬዚዳንት ትዕግስት አባተ ተፈራርመዋል፡፡

በመራዖል ከድር