የሀገር ውስጥ ዜና

የምስራቅ አፍሪካ አርብቶ አደር ኤክስፖ የመዝጊያ ሥነ-ስርዓት እየተካሄደ ነው

By Amele Demsew

February 01, 2024

አዲስ አበባ፣ ጥር 23፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) “አርብቶ አደርነት የምሥራቅ አፍሪካ ኅብረ-ቀለም” በሚል መሪ ሐሳብ ሲካሄድ የቆየው የምስራቅ አፍሪካ አርብቶ አደር ኤክስፖ ዛሬ ይጠናቀቃል።

በመዝጊያ ሥነ-ስርዓቱ የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ቀጀላ መርዳሳ፣ የመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስትር ኢንጂነር አይሻ መሀመድ እና ሌሎች ከፍተኛ አመራሮች ተገኝተዋል።

በምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት ባለስልጣን (ኢጋድ) ተባባሪነት በመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስቴር በተዘጋጀው የመጀመሪያው ቀጣናዊ ኤክስፖ የኢጋድ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች፣ የክልል እና የፌደራል ከፍተኛ አመራሮችን ጨምሮ ከ20 ሺህ በላይ ጎብኚዎች ተገኝተው ጎብኝተውታል።

በኤክስፖው አጋር አካላትም የአርብቶ አደሩን የኑሮ ዘይቤ ለማሻሻል የሚያግዙ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን ማስተዋወቃቸው ተገልጿል፡፡

ባለፉት 7 ቀናት የአርብቶ አደሩ ችግር የተነሳበት፣ መፍትሄና አቅጣጫ የተቀመጠበት እንዲሁም ከ200 በላይ ባለድርሻ አካላት የተሳተፉበት የፓናል ውይይቶች ሲካሄድ መቆየቱ ተገልጿል።

በማርታ ጌታቸውና በምንተስኖት ሙሉጌታ