አዲስ አበባ፣ ጥር 22፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በኦሮሚያ ክልል ዘንድሮ 2 ነጥብ 78 ሚሊየን ሄክታር መሬት በበጋ ስንዴ ሰብል መሸፈኑን ተችሏል ሲሉ ርዕሰ መሥተዳድር ሽመልስ አብዲሳ ገለጹ፡፡
አቶ ሽመልስ በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት÷ ቀደም ሲል ለመሸፈን ከታቀደው መሬት 105 ነጥብ 8 ሚሊየን ኩንታል ምርት እንደሚገኝ ተገምቶ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡
ይሁን እንጂ የመሬት ሽፋኑ ከዕቅድ በላይ በመሆኑና የሰብል አያያዙም ጥሩ ስለሆነ ከተገመተው በላይ ምርት እንደሚገኝ ይጠበቃል ነው ያሉት፡፡
ይህ ሽፋንም በአምስት ዓመታት ውስጥ ብቻ የተደረሰበት ነው ያሉት አቶ ሽመልስ÷ እንደ ክልልም በትጋት እየተሠራበት ያለ ዘርፍ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
በዘርፉ እየተመዘገበ ያለው ስኬትም የበጋ መስኖ ስንዴ ኢኒሼቲቭ እየተሳካ ስለመምጣቱ ማሳያ ነው ብለዋል፡፡
በመሆኑም በመሬት ሽፋን፣ በቴክኖሎጂ አጠቃቀም፣ በምርት ግብዓት አቅርቦት፣ በኤክስቴንሽን አገልግሎት፣ በምርታማነት እና በመሳሰሉት ጉዳዮች በርካታ ቀሪ ተግባራት ስላሉ በንቃት መሥራት ይጠበቃል ሲሉ አስገንዝበዋል፡፡