የሀገር ውስጥ ዜና

ኢትዮጵያ ከብሪክስ አባል ሀገራት ጋር ትብብሯን ለማጠናከር ቁርጠኛ መሆኗን ገለፀች

By Amele Demsew

January 30, 2024

አዲስ አበባ፣ ጥር 21፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ)በሩሲያ ሞስኮ በተጀመረው የብሪክስ አባል ሀገራት ተወካዮች የአመቱ የመጀመሪያ ከፍተኛ ጉባኤ ላይ ኢትዮጵያ እየተሳተፈች ነው።

በጉባኤው ላይ የብሄራዊ ባንክ ገዢ አቶ ማሞ ምህረቱ እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ ኢትዮጵያን ወክለው በመሳተፍ ላይ ናቸው።

አቶ ማሞ ምህረቱ በጉባኤው መክፈቻ ባደረጉት ንግግር ÷ኢትዮጵያ ከብሪክስ አባል ሀገራት ጋር ተቀራርቦ በመስራት ኢኮኖሚ ትብብሯን ለማጠናከር ቁርጠኛ መሆኗን ተናግረዋል።

ብሪክስ ኢትዮጵያ ለተያያዘችው የልማት ስራዎች አዳዲስ እድሎችን ይፈጥራል ያሉት አቶ ማሞ ፥ ምጣኔ ሃብትን በማዘመን ፣ የፋይናንስ ጉድለትን በመሙላት እና የኢንቬስትመንት መዋዕለንዋይን በማሳደግ ተጨማሪ የልማት ግብዐቶችን እንደሚፈጥር ገልፀዋል።

የባለብዙወገን ተቋማት አካታች ፣ ፍትሃዊ እና ውጤታማ እንዲሆኑ ማድረግ እንደሚገባም ጨምረው ማስታወቃቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

ኢትዮጵያ ብሪክስን ከተቀላቀለች ወዲህ እንዲህ ባለ ጉባኤ ላይ ስትሳተፍ የመጀመሪያዋ ሲሆን ፥ በሩሲያ ሊቀመንበርነት በመካሄድ ላይ እንደሚገኝ ታውቋል።

ጉባኤው የባለብዙ ወገን ግንኙነትን በማጠናከር ፍትሃዊ እድገት እና ደህንነትን በአለም ማስፈን በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ እየመከረ ነው።