የሀገር ውስጥ ዜና

“ፀሐይ” አውሮፕላን

By Amele Demsew

January 30, 2024

አዲስ አበባ፣ ጥር 21፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ዛሬ የጣልያን መንግሥት “ፀሐይ”ን ለኢትዮጵያ መንግሥት ያስረከቡበት የታሪካዊ ሁነት ቀን ሆኗል።

“ፀሐይ” በ1935 ዓ.ም ሄር ሉድዊግ ዌበር የተባለው ጀርመናዊ ኢንጂነር እና የንጉሱ ፓይለት በወቅቱ ከነበሩ ኢትዮጵያዊያን ጋር በመሆን በኢትዮጵያ የተሰራ የመጀመሪያው አውሮፕላን ነው። ስያሜውም የቀዳማዊ ኃይለስላሴን ልጅ ልዕልት ፀሐይን ለማሰብ የተሰጠ ነበር።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ላለፈው አንድ አመት ጊዜ ከጣልያን ጠቅላይ ሚኒስትር ጂኦርጂያ ሜሎኔ ጋር አውሮፕላኑ ወደ ኢትዮጵያ ስለሚመለስበት ሁኔታ ትልቅ ጥረት እና ሰፊ ንግግር ሲያደርጉ ቆይተዋል።

ፀሐይ ባለሁለት መቀመጫ እና ሁለትዮሻዊ መቆጣጠሪያ ያለው ብሎም የባለከፍተኛ ኃይል ሞተር ባለቤት ተደርጎ የተሰራ አውሮፕላን ነበር።

“ፀሐይ” ኮምፓስ፣ የአብራሪ መቆጣጠሪያዎች፣ ሁለት ያለ ፍሬን ማቆሚያ የተገጠሙ የማረፊያ ሽክርክሪቶች የነበሩትም ነው።

ሞተሩ ባለሰባት ሲሊንደር ዋልተር ቪነስ ሲሆን የውሃ ማቀዝቀዣ ስርዓት የነበረው የ115 የፈረስ ጉልበት ባለቤትም ነበር።

“ፀሐይ” ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በፊት በኢትዮጵያ የተሰራ ብቸኛ አውሮፕላን ነው። ፀሐይ በውስን ሃብት እና ስፍራ በጊዜው የነበሩትን አናፂዎች እውቀት እና የእጅ ጥበብ በመጠቀም የተሰራ አውሮፕላን ሲሆን የ1930ዎቹ የአቪየሽን ጥረት ማሳያ ሆኖ የተረፈን አውሮፕላን ሲል የጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት መረጃ አመልክቷል።