አዲስ አበባ፣ ጥር 21፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ከሱዳን ተፈናቅለው በአሶሳ ዞን ኩርሙክ ወረዳ ጊዜያዊ መጠለያ ጣቢያ ለሚገኙ ስደተኞ እያደረገ ያለውን እንክብካቤ በመንግሥታቱ ድርጅት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን ኮሚሽነር ፊሊፖ ግራንዴ አድንቀዋል፡፡
የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መሥተዳድር አሻድሊ ሀሰን በመንግሥታቱ ድርጅት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽነር ፊሊፖ ግራንዴ ጋር በአሶሳ ተወያይተዋል፡፡
በውይይታቸውም ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ከተቀበለቻቸው ስምምነቶች መካከል የስደተኞች አያያዝ አንዱ መሆኑን አቶ አሻድሊ አስረድተዋል፡፡
ከሱዳን ተፈናቅለው በኩርሙክ ወረዳ ጊዜያዊ መጠለያ ለሚገኙ ዜጎችም በቅርበት ክትትል እያደረግን ነው ብለዋል፡፡
የክልሉ መንግሥት ለስደተኞች እያደረገ ያለውን እንክብካቤ ያደነቁት ኮሚሽነር ፍሊፖ ግራንዴ በበኩላቸው÷ ክልሉ በተለያየ ጊዜ በሰው ሠራሽ እና በተፈጥሮ ችግሮች ምክንያት ከመኖሪያ ቀያቸው የተፈናቀሉ ዜጎችን በመንከባከብ ወደ መደበኛ ኑሯቸው እንዲመለሱ እያደረገ ያለው ሥራ ለሌሎች አርዓያ የሚሆን ነው ብለዋል፡፡
በኮሚሽነሩ የተመራው ልዑክም በሱዳን ባለው ግጭት ምክንያት ተፈናቅለው በአሶሳ ዞን ኩርሙክ ወረዳ ጊዜያዊ መጠለያ ጣቢያ የሚገኙትን ስደተኞች መጎብኘታቸውን የክልሉ ኮሙኒኬሽን መረጃ አመልክቷል።