አዲስ አበባ፣ ጥር 21፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) ያስገነባው ዘመናዊ የሚዲያ ኮምፕሌክስ ተመርቋል፡፡
በምርቃት ሥነ-ሥርዓቱ ላይ÷ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ዋና አፈ-ጉባዔ አገኘሁ ተሻገር፣ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ፣ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር)ን ጨምሮ ሌሎችም ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች፣ የሚዲያ አመራሮችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።
የሚዲያ ኮምፕሌክሱ ዘመኑ የደረሰበትን የሚዲያ ቴክኖሎጂ ያሟላና ሦስት የቴሌቪዥንና አራት የሬዲዮ ዘመናዊ ስቱዲዮዎችን ያካተተ መሆኑ ተገልጿል፡፡
በተጨማሪም÷ ለቢሮ አገልግሎት የሚሆኑ በርካታ ክፍሎች፣ የመሰብሰቢያ አዳራሾች፣ ቤተ-መጽሐፍት፣ የመዝናኛ ማዕከልና ዘመናዊ ጂምናዚየም እንዳሉት ተጠቅሷል፡፡