Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

ለሚቀጥሉት 4 ወራት ለጤና ተቋማት ብቻ 130 ሚሊየን የአፍና አፍንጫ ጭንብሎች ያስፈልጋሉ- ዶ/ር ሊያ ታደሰ

ADDIS ABABA, ETHIOPIA - APRIL 27: Lia Tadesse, Health Minister of Ethiopia, speaks to press members as breathing apparatus brought by Ethiopian Airlines from different countries, are being delivered to Ethiopian Health Ministry with a ceremony at Bole International Airport in Addis Ababa, Ethiopia on April 27, 2020. (Photo by Minasse Wondimu Hailu/Anadolu Agency via Getty Images)

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 25፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ለሚቀጥሉት 4 ወራት ለጤና ተቋማት ብቻ 130 ሚሊየን የአፍ እና አፍንጫ ሜዲካል ጭንብሎች እንደሚያስፈልጉ የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ ተናገሩ።
 
የጤና ሚኒሰትር ዶክተር ሊያ ታደሰ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ የመከላከል ስራን አስመልክቶ በሰጡት መግለጫ፥ የቫይረሱን ስርጭት ለመቀነስ የሚያስችሉ ግብአቶችን የሟሟላት ስራ በትኩረት እየተከናወነ ነው ብለዋል።
 
በተለይም በጤና ተቋማት ላይ ለሚገኙ የጤና ባለሙያዎች የሚሆኑ የሜዲካል ማስኮች አለማቀፋዊ እጥረት መኖሩን በመግለፅ፤ እንደ ሀገርም ብዙ ክፍተቶች መኖራቸውን አንስተዋል።
 
ወረርሽኙ ወደ ኢትዮጵያ ሲገባ እንደ ሀገር 4 ሚሊየን ማስክ ብቻ እንደነበር የተናገሩት ዶክተር ሊያ፥ ከዛ በኋላ በተሰሩ ስራዎች ከ7 ሚሊየን በላይ ማስኮችን ለጤና ተቋማት ማሰራጨት ተችሏል ብለዋል።
 
እንደ ሀገርም የቫይርሱን ስርጭት ለመከላከል በሚሰራው ስራ በሚቀጥሉት 4 ወራት ለጤና ተቋማት ብቻ 130 ሚሊየን ሜዲካል ማስክ እንደሚያስፈልግ መለየቱን ነው ሚኒሰትሯ የተናገሩት።
 
የማስክ እጥረትን ለመፍታት ሲባል ከውጭ ሀገር ከማስመጣት እንዲሁም በእርዳታ ከማግኘት በተጨማሪም በሀገር ውስጥ ጥራቱን የጠበቀ እና መስፈርቱን ያሟላ መስክ እንዲመረት ለማደርግም ከሚመለከታቸው ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች ጋር እየተሰራ መሆኑን አመልክተዋል።
 
በተጨማሪም የመተንፈሻ አካል አጋዥ መሳሪያ ወይም ቬንትሌተር በአለም አቀፍ ደረጃ እጥረት ያለበት መሆኑን የሚናገሩት ዶክተር ሊያ፥ ከዚህ በፊት ለዚሁ ስራ የሚውል እንደ ሀገር 22 ቬንትሌተሮች ብቻ እንደነበሩም አንስተዋል።
 
በጥገና የተስተካከሉ እና በእርዳታ የተገኙትን ጨምሮ አዲስ ግዥ ተደርጎም አሁን ላይ በሀገር አቀፍ ደረጃ 221 ቬትሌተሮች ዝግጁ መደረጋቸውንም ተናግረዋል።
 
የቫይረሱን ስርጭት ለመከላከል የኦክስጅን ምርትን በሀገር ውስጥ በስፋት እንዲመረት ማደረግ ላይም በትኩረት እየተሰራ መሆኑን እና ምርቱ የሚቀርብባቸው 3 ሺህ 600 የኦክስጅን ሲሊንደሮችም በሀገር አቀፍ ደረጃ መሰራጨታቸውን ተናግረዋል።
 
እንደ ሀገር አሁን ያለው የቫይርሱ ስርጭት መስፋትን ተከትሎ ግብእቶችን ከማሟላት በተጨማሪ የምርመራ አቅምን ማሳደግ ላይም ሰፊ ስራ እየተሰራ መሆኑንም ዶክተር ሊያ በመግለጫቸው አንስተዋል።
 
በተለይ ባለፉት 3 ሳምንታት የተመዘገበው ውጤት በጣም አስፈሪና ስርጭቱ በማህበረሰቡ ውስጥ መግባቱን የሚያሳይ በመሆኑ ምርመራን ማስፋትና የበሽታው ስርጭት ምን ላይ እንደሆነ የሚያሳየውን የአንቲ ቦዲ ምርመራ ማከናወን ትልቅ መፍትሄ ነው ብለዋል።
 
ዶክተር ሊያ አክለውም፥ የቫይረሱን ስርጭት ለመቀነስ የሰዎችን እንቅስቅሴ ከመገደብ ይልቅ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የተቀመጡ ክልከላዎችን ሁሉም ቢተገበር ስርጭቱ እንዲቀንስ ለማድረግ ሁነኛ መፍትሄ መሆኑንም ጠቅሰዋል።
 
ከቤት ሲወጡ ማስክ ማደርግ ከዚያ በላይ አካላዊ ርቀትን መጠበቅ የራስን እና የቤተሰብን ጤና ለመጠበቅ ሁነኛ መፍትሄ ነው የሚሉት ዶከተር ሊያ፥ ህብረተሰቡም ቫይረሱ በፍጥነት እየጨመረ መሆኑን በመረዳት የበኩሉን እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል።
 
በዙፋን ካሳሁን
 
#FBC
 
የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።
Exit mobile version