አዲስ አበባ፣ ጥር 20፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የአፍሪካ እና አውሮፓ ፍላጎቶች ከመቼውም ጊዜ በበለጠ የተጣጣሙ ናቸው ሲሉ የአውሮፓ ህብረት ኮሚሽን ፕሬዚዳንት ኡርሱላ ቮን ደር ሌየን ገለጹ፡፡
ፕሬዚዳንቷ በጣሊያን-አፍሪካ ጉባኤ ላይ እንደተናገሩት፤ በትብብር ጉዳይ ተጨባጭ ሁኔታ መፍጠር አስፈላጊ ነው፡፡
በአፍሪካ እና በአውሮፓ መካከል ጠንካራ ትብብር የሚፈጠርበት ጊዜ ነው ያሉት ፕሬዚዳንቷ፤ አህጉራቱ ፍላጎቶቻቸው ከመቼውም ጊዜ በላይ የተጣጣሙ ናቸው ሲሉም አክለዋል፡፡
ወደ ታዳሽና ንጹህ ኃይል መሸጋገር እና ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር መላመድ እንደሚገባ አንስተው÷ ሁላችንም የሰው ኃይላችንን ለነገ ስራ ማብቃት ይገባል ብለዋል።
በስደተኛ መተላለፊያዎች የሚደርሰውን አሳዛኝ የህይወት መጥፋት ማስቆም እና ለወጣቶችም እድሎችን ማመቻቸት እንደሚገባም ተናግረዋል፡፡
አፍሪካ እና አውሮፓን የመሬት አቀማመጣቸው ብቻ ሳሆን ለሁሉም ህዝቦቻቸው የጋራ ጥቅም ለማምጣት ያላቸው ቁርጠኝነት ጭምር እንደሚያገናኛቸው አመላክተዋል፡፡
አያይዘውም የጣሊያን እቅዶች እና የአውሮፓ ህብረት የያዛቸው ፕሮግራሞች ተደጋጋፊ መሆናቸውን አንስተዋል።
ጣሊያን የቡድን 7 ሀገራት ፕሬዚዳንት እንደመሆኗ ከአፍሪካ ጋር በትብብር መስራትን የውጭ ፖሊሲዋ ማዕከል በማድረጓ ምስጋና አቅርበዋል፡፡
የአውሮፓ ዓለም አቀፍ ግንኙነት ለአፍሪካ የ150 ቢሊየን ዩሮ የኢንቨስትመንት ዕቅድ እንደሆነና ይህም በሥራ ላይ እንዳለ ማብራራታቸውን ዘ ጋርዲያን ዘግቧል፡፡