የሀገር ውስጥ ዜና

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት የሚዲያ ኮምፕሌክስ ነገ ይመረቃል

By Amele Demsew

January 29, 2024

አዲስ አበባ፣ ጥር 20፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ያስገነባውን ዘመናዊ የሚዲያ ኮምፕሌክስ ነገ ይመረቃል፡፡

የሚዲያ ኮምፕሌክሱ ዘመኑ የደረሰበትን የሚዲያ ቴክኖሎጂ ማሟላቱ የተገለጸ ሲሆን÷ ሦስት የቴሌቪዥንና አራት የሬዲዮ ዘመናዊ ስቱዲዮዎች እንዳሉትም ተገልጿል፡፡

በተጨማሪም ለቢሮ አገልግሎት የሚውሉ ክፍሎች፣ የመሰብሰቢያ አዳራሾች ቤተ-መጽሐፍት፣ የመዝናኛ ማዕከልና ዘመናዊ ጂምናዝየም ማካተቱም ተመላክቷል፡፡

ተቋሙ ብሔራዊ መግባባት የመፍጠርና የሀገር ገፅታ ግንባታ ተልዕኮውን ለማሳካት ዜና እና ዜና ነክ መረጃዎችን ተደራሽ በማድረግ ላይ ይገኛል።

ለዚህም በመላው ሀገሪቱ 38 ቅርንጫፎችን በመክፈት በቅርቡ የጀመራቸውን ሶማሊኛ እና አፋርኛን ጨምሮ በአማርኛ፣ በኦሮምኛና በትግርኛ ቋንቋዎች የዜና ምንጭ ሆኖ ቀጥሏል።

በእንግሊዝኛ፣ በአረብኛ እና በፈረንሳይኛ ቋንቋዎችም የኢትዮጵያን ገፅታና እውነታ ለዓለም ተደራሽ እያደረገ ነው።

የስርጭትና ተደራሽነት አድማሱን በምስራቅ አፍሪካ ለማስፋት በኬንያና በጅቡቲ ቅርንጫፎችን ለመክፈት በዝግጅት ላይ እንደሚገኝም ተጠቁሟል፡፡

ኢዜአ በ1934 ዓ.ም በወቅቱ የጽሕፈት ሚኒስቴር ተብሎ ይጠራ በነበረው ተቋም፣ የጋዜጣ እና ማስታወቂያ ጽሕፈት ቤት ስር እንደ አንድ የሥራ ክፍል መቋቋሙ ይታወሳል።