አዲስ አበባ፣ ጥር 20፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ባለፉት ስድስት ወራት 4 ነጥብ 8 ቢሊየን ብር በላይ ገቢ መሰብሰቡን የሲዳማ ክልል ገቢዎች ቢሮ አስታውቋል፡፡
የቢሮው ሃላፊ አቶ ሃይሉ ጉዱራ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንዳሉት÷ በግማሽ ዓመቱ ከመደበኛ ግብር ከፋዮች እና ማዘጋጃ ቤት አገልግሎት የሚሰበሰበውን ገቢ ለማሳደግ በትኩረት ተሰርቷል፡፡
በዚህ መሰረትም 6 ነጥብ 65 ቢሊየን ብር ለመሰብሰብ ታቅዶ 4 ነጥብ 8 ቢሊየን ብር በላይ መሰብሰቡን ነው የገለጹት፡፡
የእቅዱ አፈጻጸም 73 በመቶ በላይ መሆኑን ጠቁመው÷ ከባለፋው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ1 ቢሊየን ብር ብልጫ እንዳለው አስታውሰዋል፡፡
እቅዱን ለማሳካትም አዳዲስ አሰራሮችን በመዘርጋት እንዲሁም ፖሊሲዎችን በማሻሻል ግብር ከፋዮች በወቅቱና በታማኝነት እንዲከፍሉ የማድረግ ሥራ መከናወኑን አንስተዋል፡፡
ገቢው በተለያየ ደረጃ ከሚገኙ 39 ሺህ ግብር ከፋዮች እንደተሰበሰበ ጠቁመው÷ በበጀት ዓመቱ በአጠቃላይ 13 ነጥብ 13 ቢሊየን ብር ለመሰብስብ መታቀዱን ተናግረዋል፡፡
በቀጣይ የገቢ ሥወራን መቆጣጠር፣ የተሻለ ዘመናዊ አሰራር መዘርጋት፣ ሀሰተኛ ደረሰኝን መከላከል እና መረጃ አያያዝን ማዘመን ላይ በትኩረት እንደሚሰራ ጠቅሰዋል፡፡
በመላኩ ገድፍ