የሀገር ውስጥ ዜና

የኮምቦልቻ ከተማ ነዋሪዎች ሰላማቸውን ለማስጠበቅ ያሳዩት ቁርጠኝነት የሚደነቅ ነው – አቶ አረጋ ከበደ

By Amele Demsew

January 28, 2024

አዲስ አበባ፣ ጥር 19፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በኮምቦልቻ ከተማ አሥተዳደር ከ580 ሚሊየን ብር በላይ በሆነ ወጪ የተሠሩ የተለያዩ የልማት ፕሮጀክቶች ለአገልግሎት ክፍት ሆነዋል።

የልማት ፕሮጀክቶች የአማራ ክልል ርዕሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደን ጨምሮ ሌሎች የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች በተገኙበት ነው ተመርቀው ለአገልግሎት ክፍት የሆኑት።

በከተማዋ ከተመረቁ ፕሮጀክቶች መካከል የኮምቦልቻ መናኸሪያ፣ ትምሕርት ቤት እና የተለያዩ የኢንቨስትመንት ልማቶች ይገኙበታል።

አቶ አረጋ ከበደ በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት÷ ኮምቦልቻ ሰፊ የመልማት አቅም ያላት ከተማ በመሆኗ በከተማዋ ተጀምረው ያልተጠናቀቁ የልማት ሥራዎችን ለማስቀጠል መሥራት ይገባል፡፡

ማኅበረሰቡ ሰላሙን በመጠበቅ ለልማት ያሳየው ቁርጠኝነት የሚደነቅ ነው ሲሉም ነው የገለጹት፡፡

በዛሬው ዕለት ተመርቀው ለአገልግሎት የበቁ ፕሮጀክቶችም ችግር ፈቺ መሆናቸውን ርዕሰ መስተዳደሩ ጠቁመዋል።

በኮምቦልቻ ከተማ አሥተዳደር በ1 ነጥብ 6 ቢሊየን ብር የተለያዩ የልማት ሥራዎች እየተከናወኑ እንደሚገኙ መጠቀሱንም አሚኮ ዘግቧል፡፡