አዲስ አበባ፣ ጥር 19፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የክልል ርዕሳነ መስተዳድሮች ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የከበረውን የፋኦ አግሪኮላ ሜዳልያ በመሸለማቸው የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
የሐረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ÷ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተባበሩት መንግሥታት የምግብ እና የእርሻ ድርጅት የከበረውን የፋኦ አግሪኮላ ሜዳልያ በመሸለማቸው የተሰማቸውን ደስታ ገልፀዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በምግብ ዋስትና እና በተመጣጠነ የምግብ አቅርቦት ላሳዩት ርዕይ፣ አመራር እና ቁርጠኝነት፣ ብሎም ፈጣን፣ ተለዋዋጭ እና ፈታኝ በሆነው ከባቢያዊ ሁኔታ በስንዴ ምርት ራስን ለመቻል በተከተሉት ፈጠራዊ መፍትሔ የተበረከተላቸው ዕውቅናም እንደሀገር የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ ተጨማሪ መነሳሳትን የሚፈጥር ነው ብለዋል።
በተመሳሳይ የሶማሌ ክልል ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) በምግብ ዋስትና እና በተመጣጠነ የምግብ አቅርቦት ላሳዩት ርዕይ እና በሳል አመራር፣ በተባበሩት መንግሥታት የምግብ እና የእርሻ ድርጅት “የፋኦ አግሪኮላ” ሜዳልያ በመሸለማቸው የተሰማውን ደስታ ገልጿል፡፡