Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

ጠ/ሚ ዐቢይ (ዶ/ር) በኢትዮጵያ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ አብነት የሚሆን ሥራ አከናውነዋል- የተመድ የኢንዱስትሪ ልማት ድርጀት ዳይሬክተር

አዲስ አበባ፣ ጥር 19፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በኢትዮጵያ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ አብነት የሚሆን ሥራ አከናውነዋል ሲሉ የተመድ የኢንዱስትሪ ልማት ድርጅት ዳይሬክተር ጀነራል ገርድ ሙለር ገለጹ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተባበሩት መንግሥታት የምግብ እና የእርሻ ድርጅት በሮም ጣልያን በተሰናዳ ክብረ በዓል የከበረውን የፋኦ አግሪኮላ ሜዳልያ ተሸልመዋል።

የተመድ የኢንዱስትሪ ልማት ድርጅት ዳይሬክተር ጀነራል ገርድ ሙለር ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) በዘርፉ ባስገኙት ውጤት ለተደረገላቸው ሽልማት የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

በመልዕክታቸውም÷ኢትዮጵያ የምግብ ዋስትናን በማረጋገጥና በተመጣጠነ የምግብ አቅርቦት ባስገኘችው አመርቂ ውጤት መደሰታቸውን ገልጸዋል፡፡

ባለፉት ጥቂት ዓመታት ኢትዮጵያ በዘርፉ አበረታች ውጤት አስመዝግባለች ያሉት ዳይሬክተር ጀነራሉ÷ ለዚህ ማሳያም ኢትዮጵያ የስንዴ እህል ምርትን በእጥፍ በማሳደግ ራሷን ችላ ወደ ውጪ መላክ ጀምራለች ብለዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) በኢትዮጵያ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ አብነት የሚሆን ሥራ አከናውነዋል ሲሉም ተናግረዋል፡፡

በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ መሪነት በዘርፉ የተገኘው ውጤት ለመላው አፍሪካ በአርኣያነት የሚወሰድ መሆኑንም ነው የገለጹት፡፡

የተመድ የኢንዱስትሪ ልማት ድርጅት በቀጣይ በዘርፉ ለሚከናዎኑ ሥራዎች ለኢትዮጵያ የሚያደርገውን ድጋፉ አጠናክሮ እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል፡፡

Exit mobile version