አዲስ አበባ፣ ጥር 19፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የምግብ ሉዓላዊነት ጉዟችንን በፅናት እናስቀጥላለን ሲሉ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተባበሩት መንግሥታት የምግብ እና የእርሻ ድርጅት በሮም ጣልያን በተሰናዳ ክብረ በዓል የከበረውን የፋኦ አግሪኮላ ሜዳልያ ተሸልመዋል።
ሽልማቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) በምግብ ዋስትና እና በተመጣጠነ የምግብ አቅርቦት ላሳዩት ርዕይ፣ አመራር እና ቁርጠኝነት፣ ብሎም ፈጣን፣ተለዋዋጭ እና ፈታኝ በሆነው ከባቢያዊ ሁኔታ በስንዴ ምርት ራስን ለመቻል በተከተሉት ፈጠራዊ መፍትሔ ዕውቅና ለመስጠት የተበረከተ ነው፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) በዚህ ወቅት ባደረጉት ንግግር÷ለተመድ የምግብ እና የግብርና ድርጅት የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ለምናደርገው ጥረት የከበረውን አግሪኮላ ሜዳልያ ስላጎናፀፈን ምስጋናዬን ለመግለፅ እወዳለሁ ብለዋል፡፡
ከፍ ያለ ጠቀሜታ ባላቸው እና የኢንዱስትሪ ግብዓት በሆኑ የግብርና ምርቶች ላይ ማተኮራችን ተስፋ ሰጪ ውጤቶች እያስገኘልን ይገኛልም ነው ያሉት፡፡
የምግብ ሉዓላዊነት ጉዟችንን በፅናት እናስቀጥላለን ሲሉም ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው አስፍረዋል፡፡