Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ የህልውና እና ብሔራዊ ጥቅምን የማስጠበቅ ጉዳይ መሆኑ ተመለከተ

አዲስ አበባ፣ ጥር 19፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ ለቀጣናው ሀገራት የህልውና እና ብሔራዊ ጥቅምን የማስጠበቅ ጉዳይ መሆኑን በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አመራሮች ገለጹ።

የኮሚቴው ምክትል ሰብሳቢ ፈትሂ ማሕዲ(ዶ/ር) እንደገለጹት፥ ኢትዮጵያ በከፍኛ ፍጥነት እያደገ ያለ ኢኮኖሚና የህዝብ ቁጥር ያላት በመሆኗ አማራጭ ወደብ የግድ ያስፈልጋታል።

የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ማደግ፣ የወጪና ገቢ ንግድ መጨመርን ተከትሎ አንድ ወደብ ብቻ ኢኮኖሚዋን ሊሸከም አይችልም ነው ያሉት ።

ኢትዮጵያ የባህር በር የመፈለጓ መሰረታዊ መነሻ የህልውና ጉዳይ ነው ያሉት ምክትል ሰብሳቢው ከሶማሌላንድ ጋር ከተፈረመው የመግባቢያ ስምምነት ባሻገር ሌሎች ጥረቶችም ይቀጥላሉ ብለዋል።

ኢትዮጵያ የባህር በር ማግኘቷ የግድ ቢሆንም የምትከተለው መርህ ሰላማዊ አማራጭ መሆኑን በመንግስት ደረጃ መገለጹንም ነው ፈትሂ (ዶ/ር)የተናገሩት።

የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባል ባለው ባዬ (ዶ/ር)÷ኢትዮጵያ በምስራቅ አፍሪካ በህዝብ ቁጥርም በኢኮኖሚ እድገትም ቀዳሚ መሆኗን ገልጸው ከዚህ አኳያ እያደገ የመጣውን ፍላጎት በብቃት የሚሸከም ወደብ እንደሚያስፈልጋት ተናግረዋል።

የኮሚቴው አመራሮች ቀይ ባህር የዓለም ንግድ ዋነኛ መተላለፊያ፣ የኃያላን የትኩረት ነጥብ መሆኑን ገልጸው ኢትዮጵያ ካላት ቅርበት አንጻር ብሔራዊ ጥቅሟን ለማስጠበቅ በዝምታ አትቀመጥም ብለዋል።

ከወጪ ንግዷ ባሻገር ወደ ሀገር ውስጥ የሚገቡ አንገብጋቢ የሆኑ እንደ መድሃኒት፣ ማዳበሪያ፣ ነዳጅና መሰል ምርቶችም የሚጓጓዙት በዚሁ መስመር በመሆኑ ተለዋዋጭ ሁኔታዎች ያሳስቧታልም ነው ያሉት።

ኢኮኖሚያዊ ህልውናዋን እና ሉዓላዊ ደህንነቷን ለማስከበር የባህር ኃይሏ የሚንቀሳቀስበት የባሀር በር እንዲሁም ለንግድ አማራጭ ወደብ የግድ እንደሚያስፈልጋት መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

Exit mobile version