Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

ፋና በህዝቦች መካከል ሰላምና ዲሞክራሲ እንዲሰፍን ገንቢ ሚናውን እየተወጣ ነው – ለገሰ ቱሉ(ዶ/ር)

አዲስ አበባ፣ ጥር 19፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት በህዝቦች መካከል ሰላምና ዲሞክራሲ እንዲሰፍን ገንቢ ሚናውን እየተወጣ ነው ሲሉ የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡
ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ያስገነባውን አዲስ የፋና ላምሮት ዘመናዊ ስቱዲዮ ዛሬ አስመርቋል፡፡
ሚኒስትሩ በዚሁ ወቅት እንዳሉት÷ ፋና ህዝቦች ለሀገር ግንባታ በሚበጅ መልኩ ወደ አንድ እንዲመጡ እንዲሁም ሰላምና ዲሞክራሲ እንዲሰፍን ሚናውን እየተወጣ ይገኛል፡፡
ፋና በኢትዮጵያ የሚዲያ ኢንዱስትሪ በተለይም በሬዲዮ ዘርፍ ቀዳሚ መሆኑ ሁሉም የሚመሰክረው ነው ሲሉም አክለዋል፡፡
አሁን ደግሞ በሀገራችን ካሉ የቴሌቪዥን ጣቢያዎች በተሻለ አቀራረብና በተሻለ ይዘት እየመጣ ነውም ነው ያሉት፡፡
በቀጣይም በአዳዲስ አቀራረብና ይዘት ከመጣ ፋና በማሳወቅ፣ በማስተማርና መረጃ በመስጠት ተወዳዳሪ የሚዲያ ኢንዱስትሪ እንደሚሆን አምናለሁም ብለዋል ፡፡
በተለይም እንደ ፋና ቀለማትና ፋና ላምሮት የኪነጥበብ ባህልን ከማሳደግ ባለፈ ተሰጥኦ ያላቸው ሰዎችን ወደ ህዝቡ እንዲመጡና ችሎታቸው እንዲዳብር የማገዝ ስራ በመስራት የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች ወደ ተሻለ ቦታ እንዲደርሱ በማድረግ ላይ ይገኛሉ ሲሉም ገልጸዋል፡፡
በዚህም የሀገር ግንባታና የትውልድ ግንባታ ሚናውን እየተወጣ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡
ኮርፖሬቱ እጅግ አነስተኛ ከሆነች ጎጆ ተነስቶ ዛሬ ሦስት አራት አገልግሎት የሚሰጥ ሱቱዲዮ ለመገንባት በመብቃቱ መደሰታቸውንም ገልጸዋል፡፡
ተቋሙን ለዚህ ስኬት ላበቁ የኮርፖሬቱ አመራሮች፣ ሙያተኞችና ባለድርሻአካላት ምስጋና ያቀረቡ ሲሆን የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎትም ተገቢውን ድጋፍ እንደሚያደርግ ገልጸዋል፡፡
በአመለወርቅ

ደምሰው

Exit mobile version