የሀገር ውስጥ ዜና

የፋና ላምሮት ስቱዲዮ የተቋሙን አቅም በማሳደግ ወቅታዊና ታኣማኒ መረጃዎችን በተለየ አቀራረብ ለማስተላለፍ ያስችላል – አቶ አደም ፋራህ

By Melaku Gedif

January 28, 2024

አዲስ አበባ፣ ጥር 19፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ፋና ብሮካስቲንግ ኮርፖሬት ያስገነባው አዲስ የፋና ላምሮት ዘመናዊ ስቱዲዮ የተቋሙን አቅም በማሳደግ ወቅታዊና ታኣማኒ መረጃዎችን በተለየ አቀራረብ እንዲያስተላልፍ ያስችለዋል ሲሉ የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ አደም ፋራህ ገለጹ፡፡

ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ያስገነባውን አዲስ የፋና ላምሮት ስቱዲዮ በዛሬው ዕለት እያስመረቀ ነው፡፡

በምርቃ ሥነ-ሥርዓቱ አቶ አደም ፋራህን ጨምሮ የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር)፣ የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴዔታ ከበደ ዴሲሳ ፣ተጋባዥ እንግዶች እና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል፡፡

አቶ አደም ፋራህ በሥነ-ሥርዓቱ ላይ ባደረጉት ንግግር÷የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን አቅም ይበልጥ የሚያሳድገው የፋና ላምሮት ስቱዲዮ ደረጃውን በጠበቀ መልኩ ተገንብቶ ለምረቃ በመብቃቱ እንኳን ደስ አላችሁ ብለዋል፡፡

አዲሱ የፋና ላምሮት ዘመናዊ ስቱዲዮ ፋና ከዚህ ቀደም የሚታወቅባቸውን ወቅታዊ፣አስተማሪ እና አዝናኝ ፕሮግራሞችን በበለጠ ከፍታ ለብዙ ተመልካቶች እንዲያስተላልፍ ያስችለዋል ነው ያሉት፡፡

ፋና እንደ ንግድ ሚዲያ ለትርፋማነት ብቻ የሚሰራ ሳይሆን ተደራሽነቱን እያሰፋ እና አሰራሩን እያዘመነ ፈጠራ በታከለበት መልኩ በልዩ መረጃ አቀራረብ እና ብስለት የመተቸት፣ የማጋለጥ፣ የማረም፣ የማዝናናት እና የሀገር ገጽታ ግንባታ ሥራን በብቃት ማከናወን ይጠበቅበታል ብለዋል፡

ለጠንካራ ሀገረ መንግስት ግንባታ እና የሀገር ፍቅርና ክብር ያለው ትወልድን ለማነጽ ሚዲያ ትልቅ ሚና እንዳለውም አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡

መንግስት ሚዲያ ለዴሞክራዊ ሥርዓት እና ለሀገር ግንባታ ያለውን ወሳኝ ሚና በሚገባ ይረዳል ያሉት አቶ አደም÷ ለዚህም እንደ ፋና ያሉ ሙያዊ ነጻ ነታቸውን ጠብቀው በሃላፊነት የሚሰሩ ሚዲያዎች ያስፈልጋሉ ብለዋል፡፡

ሚዲያዎች በሀገረ መንገስት ግንባታ ሒደት ውስጥ ትኩረታቸውን በአሰባሳቢ ትርክት እና ትውልድ ግንባታ ሥራ ላይ ሊያደርጉ እንደሚገባ ጠቅሰዋል፡፡

ባለብዝሃ መልክ በሆነችው ኢትዮጵያ የሚዲያ ይዘቶች ሕዝቦችን ከሀገራቸውም ሆነ እርስ በእርሳቸው የሚያስተዋውቁ እና አብሮነት እና ሕብረ ብሄራዊነትን የሚያጠናክሩ መሆን አለባቸውም ብለዋል፡፡

ሚዲያዎች በመንግስት አሰራሮች ውስጥ ግድፈቶች እንዲታረሙ የማሳየት እና ተጠያቂነት እንዲሰፍን የማገዝ ሚናቸውን መወጣት እንዳለባቸውም አስገንዝበዋል፡፡

የአካታችነት፣ ሚዛናዊነት፣ ወድማማችነት እና እህትማማችነትን እሴት እንዲያዳብር የማድረግ እና አዎንታዊ የሆነ ዘላቂ ሰላም እንዲረጋገጥ የሕብረተሰቡን አስተሳሰብ የመቅረጽ ኃላፊነት እንዳለባቸውም ጠቁመዋል፡፡

ይሁን እንጂ መደበኛ ሚዲዎች ሚናቸውን ለመወጣት በሚያደርጉት ጥረት ያለንበት የበይነ መረብ ዘመን እና በሀገራችን የተፈጠረው አውድ እድልም ፈተናም ይዞ የመጣበት ሁኔታ መኖሩን አስረድተዋል፡፡

ከዕድል አንጻር ያለንበት ዘመን ለሚዲዎች አመቺ እና ተደራሽነትን በማስፋት ተልዕኳቸውን እንዲወጡ ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል ነው ያሉት፡፡

በአንጻሩ ሀሰተኛ የሆኑ መረጃዎች ስርጭት በመስፋፋታቸው እና ከፍተኛ ስጋት በመደቀናቸው መገናኛ ብዙሃን እና በዜጎች መካከል ያለው የመተማመን ደረጃ እየተሸረሸረ መጥቷል ብለዋል፡፡

ሚዲያዎች የሀገርን ብሄራዊ ጥቅም መጠበቅ እና እውነትን ከሀቅ እና ከፍትሃዊነት መዘገብ እና ሁሌም የጋዜጠኝነት መርሕ እና ሙያዊ ሥነ ምግባር መተግበር ያስፈልጋል ሲሉም ገልጸዋል፡፡

በመላኩ ገድፍ