አዲስ አበባ፣ ጥር 19፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ያስገነባውን አዲስ የፋና ላምሮት ስቱዲዮ በዛሬው ዕለት አስመርቋል፡፡
በምረቃ መርሐ ግብሩ የብልፅግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ አደም ፋራህ፣ የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ(ዶ/ር)፣የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ ከበደ ዴሲሳ ፣ተጋባዥ እንግዶች እና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል፡፡
ስቱዲዮው በዋናነት የመዝናኛ ፕሮግራሞችን እና አሳታፊ መድረኮችን እንዲያስተናግድ ታስቦ የተገነባ ነው፡፡
አዲሱ ስቱዲዮ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ተጨማሪ ጥንካሬን እንደሚያላብስ ተመላክቷል።
ፋና እስካሁን ድረስ ተወዳጁን ፕሮግራም ፋና ላምሮትን ጨምሮ በርካታ ሰዎች የሚገኙበት የውይይት መድረኮችን ከዋናው መሥሪያ ቤት ውጭ በተከራየው ሕንፃ ወደ ተመልካቾች ሲያደርስ ቆይቷል፡፡
ሕንፃው ለሚዲያ ታስቦ የተሰራ ባለመሆኑ ግን ለሥራው በሚፈለገው ልክ ምቹ አልነበረም፡፡
ተቋሙ ለሕንፃ ኪራይ በየወሩ ከፍተኛ ገንዘብ ለማውጣትም ይገደድ ነበር፡፡
አዲሱ ስቱዲዮ ታዲያ ይህን ወጪ የሚያስቀርና ፋና በተሻለ አቀራረብ ወደ ተመልካቾቹ እንዲደርስ የሚያስችለው ነው፡፡