Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

አሜሪካ ለቱርክና ግሪክ የጦር ጄቶች እንዲሸጡ ፈቀደች

አዲስ አበባ፣ ጥር 18፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የጆ ባይደን አስተዳደር የጦር ጄቶች ለቱርክ እና ለግሪክ እንዲሸጡ የቀረበውን የውሳኔ ሃሳብ አፅድቋል፡፡

የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤትና የመከላከያ ደህንነት ትብብር ኤጀንሲ እንደገለፁት፤ በስምምነቱ መሰረት ኤፍ-16 ተዋጊ ጄቶች ለቱርክ እንዲሁም ኤፍ-35 ተዋጊ ጄቶች ለግሪክ የሚሸጡ ይሆናል፡፡

23 ቢሊዮን ዶላር የሚያወጣው የኤፍ 16 ተዋጊ ጄቶች ሽያጭ ውሳኔ ስዊድን የሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃል ኪዳንን (ኔቶ) እንድትቀላቀል ቱርክ ፈቃዷን መስጠቷን ተከትሎ የተደረሰ ስምምነት መሆኑም ተመላክቷል፡፡

ቱርክ ኤፍ-16 ተዋጊ ጄቶችን ከአሜሪካ ለመግዛት በ2021 ጥያቄ ያቀረበች ቢሆንም የስዊድንን ወደ ኔቶ መቀላቀል እውቅና ባለመስጠቷ ጥያቄዋ በአሜሪካ ውድቅ ሆኖ መቆየቱ ተገልጿል፡፡

በተመሳሳይ አሜሪካ ቀደምት የኔቶ አባል ሀገር ለሆነችው ግሪክ የ8 ነጥብ 6 ቢሊዮን ዶላር የኤፍ-35 ተወጊ ጄት ሽያጭ ስምምነት የፈፀመች ሲሆን ስምምነቱ የግሪክን የአየር ሀይል የበለጠ ያጠናክራል ተብሏል፡፡

ይህም የአሜሪካን የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ አላማዎችን እና ብሔራዊ ደህንነት የበለጠ እንደሚያጠናክር የአሜሪካ መከላከያ ደህንነት ትብብር ኤጀንሲ መግለፁን ዘ ናሽናል ዘግቧል፡፡

Exit mobile version