የሀገር ውስጥ ዜና

ተፈናቃይ ነን በማለት በሀሰተኛ ሰነድ ከ8 ሚሊየን ብር በላይ ጉዳት አድርሰዋል የተባሉ ግለሰቦች እንዲከላከሉ ብይን ተሰጠ

By Amele Demsew

January 26, 2024

አዲስ አበባ፣ ጥር 17፣ 2016 (ኤፍቢ ሲ) ከሶማሌ ክልል ተፈናቃይ ነን በማለት በሀሰተኛ ሰነድ በመንግስት ላይ ከ8 ሚሊየን ብር በላይ ጉዳት አድርሰዋል የተባሉ 20 ግለሰቦች እንዲከላከሉ የኦሮሚያ ክልል ሸገር ከተማ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ወንጀል ችሎት ብይን ሰጠ።

የክልሉ ፍትህ ቢሮ የሙስና ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዐቃቤ ሕግ በነሃሴ ወር 2015 ዓ.ም ሶስት ክሶችን ካቀረበባቸው 50 ተከሳሾች መካከል ብርሃኑ ግርማ፣ ደረጄ ጌታቸው፣ ዱቦ ፉፋ፣ ሙሳ አብዲን ጨምሮ ሌሎች የሚገኙበት ሲሆን በቁጥጥር ስር ውለው ፍርድ ቤት የቀረቡት ግን 21 ብቻ ናቸው።

ዐቃቤ ሕግ በ1996 ዓ.ም የወጣውን የወንጀል ህግ አንቀጽ 32 ንዑስ ቁጥር 1 ሀ እና አንቀጽ 696 (ሐ) ስር የተመለከተውን እንዲሁም የሙስና አዋጅ ቁጥር 881/2007 አንቀጽ 4 ንዑስ ቁጥር 4፣ አንቀጽ 23 (2.3) እና አንቀጽ 32 (3.2) ላይ የተመላከተውን ድንጋጌ ተላልፈዋል በማለት የክስ ዝርዝር አቅርቦባቸዋል።

በቀረበው በአንደኛው ክስ ላይ እደተመላከተው ከ1ኛ እስከ 5ኛ ተራ ቁጥር የተጠቀሱት ተከሳሾች ከሶማሌ ክልል በግጭት ምክንያት ከኦሮሚያ ክልል አዋሳኝ አካባቢ የተፈናቀሉ 1 ሺህ 854 ዜጎች የተፈናቃይ ኮሚቴ ሆነው ሲሰሩ ከአደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን በተጻፈ የእርዳታና ድጎማ ደብዳቤ መነሻ የአ/አ ከተማ አስተዳደር ካቢኔ በወቅቱ በኮዬ ፌጬ አካባቢ ለተፈናቃዮች ቤት እንዲሰራ በወሰነው ውሳኔ መሰረት ለተፈናቃዮች የድጋፍና ድጎማ ስራ ሲጀምር በጥር 16 ቀን 2010 ዓ.ም ተፈናቃይ ያልሆኑ ግለሰቦች በሀሰተኛ ጊዜያዊ መታወቂያና ሰነድ ዝርዝር እንዲካተት አድርገዋል በሚል ተጠቅሷል።

በተለይም ተፈናቃይ ዜጎችን የመደጎምና የመኖሪያ ቤት የመስጠት ሂደት ውስጥ ከ5ኛ እስከ 30ኛ ተራ ቁጥር የተጠቀሱ ተከሳሾች ተፈናቃይ ነን በማለት ሀሰተኛ የተፈናቃይ ጊዜያዊ መታወቂያና የተለያዩ ሀሰተኛ ሰነዶችን በማቅረብ በማጭበርበር በእርዳታ ድጎማው ተጠቃሚ እንዲሆኑ መደረጉ በክሱ ዝርዝር ተመላክቷል።

በሌላኛው ክስ ደግሞ ከ31ኛ እስከ 50ኛ ተራ ቁጥር የተካተቱ ተከሳሾች በተለያየ ጊዜ ሀሰተኛ የተፈናቃይ መታወቂያዎችን እና ከሪፍት ቫሊ ዩኒቨርሲቲ ዋናው ካንፓስ የተሰጡ የሚመስሉ ሀሰተኛ ሰነዶችን በተለያዩ ስም ዝርዝሮች በማቅረብ ተሳትፎ ያላቸው ተከሳሾች መኖራቸው ተጠቅሷል።

በዚህ መልኩ ተከሳሾቹ በጥቅም በመመሳጠር ተፈናቃይ ሳይሆኑ ነን በማለት እና ተፈናቃይ እንደሆኑ የሚገልጹ ቅጾችን በመሙላት እና በማስሞላት ጭምር ባደረጉት ተሳትፎ በኮዬ ፈጬ አካባቢ እያንዳንዳቸው 705 ሺህ 225 ብር ከ04 ሳንቲም የሚገመት መኖሪያ ቤት በመውሰድ እንዲሁም 19 ሺህ 600 ብር ድጎማ እያንዳንዳቸው በተለያየ ጊዜ በመቀበል በተፈጸመ የማጭበርበር የሙስና ወንጀል ድርጊት በመንግስት ላይ 8 ሚሊየን 697 ሺህ 876 ብር ከ08 ሳንቲም ጉዳት አድርሰዋል በማለት ዐቃቤ ሕግ የተከሳሾቹን ሚና ጠቅሶ ክስ መስርቶባቸው ነበር።

ይሁንና ፍርድ ቤት የቀረቡና ክሱ እንዲደርሳቸው የተደረጉ 21 ተከሳሾች በክሱ ላይ የተጠቀሰውን የወንጀል ድርጊት አለመፈጸማቸውን ጠቅሰው የዕምነት ክህደት ቃላቸውን በመስጠታቸው ዐቃቤ ሕግ 14 የሰው ምስክሮችና ለወንጀሉ መፈፀም ያስረዳሉ ያላቸውን የተቋማት እና የተለያዩ የሰነድ ማስረጃዎችን አቅርቧል።

ፍርድ ቤቱ የዐቃቤ ሕግ የሰውና የሰነድ ማስረጃዎችን ከመረመረ በኋላ 20 ተከሳሾች በቀረቡባቸው የክስ ድንጋጌዎች እንዲከላከሉ ዛሬ በዋለው ችሎት ብይን ሰጥቷል።

በክስ መዝገቡ ላይ በ21ኛ ተራ ቁጥር ላይ የተጠቀሰው ተከሳሽ ግን በነጻ ተሰናብቷል።

ፍርድ ቤቱ የሁለተኛ ክስ ጭብጥ ከአንደኛ ክስ ጋር ተመሳሳይነት ያለው መሆኑን ጠቅሶ ሁለተኛ ክስ ከአንደኛው ክስ ጋር እንዲጠቃለል አድርጓል።

ተከላከሉ የተባሉ 20 ተከሳሾችን በሚመለከት የመከላከያ ማስረጃ ካላቸው ለመጠባበቅ ለየካቲት 11 ቀን 2016 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።

በታሪክ አዱኛ