የሀገር ውስጥ ዜና

የግብርናና የጤና ዘርፎችን የሚያግዙ ድሮኖችን የሰሩ ወጣቶች

By Amele Demsew

January 27, 2024

አዲስ አበባ፣ ጥር 17፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ በስፔስ ሳይንስ ኢንስቲትዩት የምርምር ስራዎች ክፍል የሚሰሩት ወጣት ዳዊት ከፍያለው እና ጓደኞቹ የግብርና እና የጤና ዘርፎችን የሚያግዙ አምስት ድሮኖችን ሰርተዋል፡፡

ወጣቶቹ የሰሯቸው ድሮኖች የመንገድ መሰረተ ልማት ባልተሟላላቸው አካባቢዎች ላይ መድሃኒቶችን ተሸክመው ሊያጓጉዙ የሚችሉና የግብርናው ዘርፍ የሚያዘምኑ ሲሆን በማሳዎች ላይ የፀረ አረም መድሃኒቶችን መርጨት የሚችሉ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ዳዊት ከፍያለው እና ጓደኞቹ ከነዚህ ድሮኖች በተጨማሪ ማሻሻያ ያደረጉባቸውን አውሮፕላኖችን መስራታቸውን ገልፀዋል፡፡

ለዚህም መንደርደር ሳያስፈልገው እንደ ሄሊኮፕተር ከመሬት በመነሳት እንደ አውሮፕላን መብረር የሚችል የፈጠራ ስራቸው ሌላው ውጤታቸው መሆኑን አስረድተዋል።

ለአቪዬሽን ዘርፉ ልህቀት እና ተወዳዳሪነት ፈጠራን እና የፈጠራ ባለሙያዎችን ማበረታታትና መደገፍ እንደሚገባ የሚያነሱት የፈጠራ ባለሙያዎቹ፤ ባለፉት ዓመታት መንግስት ለአቪዬሽን ዘርፉ የሰጠውን ልዩ ትኩረት አድንቀዋል።

በቅርቡም በኢትዮጵያ ሳይንስ ሙዚየም የተዘጋጀው የአቪዬሽን ኢኖቬሽን 2016 ኤክስፖ፥ ስራዎቻቸውን እንዲያስተዋውቁ፣ የሌሎችን ስራ በማየት ልምዶችን እንዲወስዱ እና የስራ እድል የፈጠረላቸው መሆኑን ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ተናግረዋል።

የፈጠራ ባለሙያዎቹ በቀጣይ ከትምህርት ተቋማቸው ጋር በመሆን ድሮኖቹን በስፋት የማምረት እና የማከፋፈል ዕቅድ ይዘው እየሰሩ እንደሚገኙም ገልጸዋል።

በመራኦል ከድር