ዓለምአቀፋዊ ዜና

በቀይ ባህር ላይ የሚካሄደው የንግድ እንቅስቃሴ 42 በመቶ ቀንሷል ተባለ

By Mikias Ayele

January 26, 2024

አዲስ አበባ፣ ጥር 17፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የሁቲ አማፂያን በሚፈፅሙት ጥቃት ምክንያት በቀይ ባህር ላይ የሚካሄደው የንግድ እንቅስቃሴ 42 በመቶ መቀነሱን የተባበሩት መንግሰታት ድርጅት (ተመድ) አስታወቀ፡፡

የንግድ እንቅስቃሴው መቀነስ በሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነት ምክንያት በችግር ውስጥ የሚገኙትን የጥቁር ባህር እና የፓናማ ቦይ የንግድ እንቅስቃሴዎችን የበለጠ ጫና ውስጥ እያስገባቸው መሆኑም ተመላክቷል።

በተመድ የንግድ እና ልማት ኮንፈረንስ ኃላፊ ጃን ሆፍማን እንደተናገሩት÷ በቀይ ባህር መርከቦች ላይ የሚፈፀሙ ጥቃቶች በዓለም የጂኦ ፖለቲካ እና የንግድ እንቅስቃሴ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እያሳደረ ነው፡፡

ቀይ ባህር የዓለምን 80 በመቶ የንግድ እንቅስቃሴ እንደሚሽፈን ገልጸው÷ ባለፉት ሶስት ወራት የሁቲ አማፂያን ጥቃት ፈጽመው የመርከብ ፍንዳታ አደጋ ይደርሳል በሚል ስጋት የመርከበኞች እንቅስቃሴ መገታቱን አስረድተዋል፡፡

በቀይ ባህር ቀውስ ምክንያትም ከአውሮፓ፣ ሩሲያ እና ዩክሬን የሚላኩ ሸቀጣሸቀጦችን ማዘዋወር አለመቻሉ ነው የተገለፀው፡፡

በዚህም እንደ ምስራቅ አፍሪካ፣ ደቡብ እስያ፣ ደቡብ ምስራቅ እስያ እና በምስራቅ እስያ ቀጠናዎች የምግብ ዋስትና ስጋትን ሊያስከትል እንደሚችል መገለፁን ሲጂቲኤን ዘግቧል፡፡