የሀገር ውስጥ ዜና

ከ1 ቢሊየን ብር በላይ ገንዘብ ከምዝበራ ማዳን መቻሉ ተገለጸ

By Melaku Gedif

January 26, 2024

አዲስ አበባ፣ ጥር 17፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ባለፉት ስድስት ወራት ከ1 ቢሊየን ብር በላይ ከምዝበራ ማዳን መቻሉን የፌዴራል ሥነ- ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን አስታወቀ።

የኮሚሽኑ አስቸኳይ ሙስና መከላከል መሪ ሥራ አስፈፃሚ ገዛኽኝ ጋሻው በስድስት ወራት ውስጥ የተካሔደውን አስቸኳይ የሙስና መከላከል ተግባር በተመለከተ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

በዚህም በበጀት ዓመቱ ስድስት ወራት በሀገር አቀፍ ደረጃ 231 አስቸኳይ የሙስና መከላከል ስራዎች ተሰርተዋል ነው ያሉት።

በመከላከል ተግባሩ ከአንድ ቢሊየን ብር በላይ ገንዘብና ከ 21 ሚሊየን ካሬ ሜትር በላይ የገጠርና የከተማ መሬት ከምዝበራ ማዳን መቻሉን ተናግረዋል።

በአስቸኳይ ሙስና መከላከል ሥራው በምዝበራ ከተያዘው ሃብት ጋር ግንኙነት ያላቸውን አካላት ተጠያቂ ለማድረግ እየተሰራ እንደሆነ መጠቆማቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

ህብረተሰቡ መረጃዎችንና ማስረጃዎችን በመስጠት ረገድ የነበረው ሚና የሚመሰገን እንደነበር ጠቁመው÷ በቀጣይም በፀረ ሙስና ትግሉ ላይ ንቁ ተሳትፎ ማድረግ እንደሚገባ አስታውቀዋል።