አዲስ አበባ፣ ጥር 17፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በ2016/17 ምርት ዘመን የአፈር ማዳበሪያ ለአማራ ክልል አርሶ አደሮች በወቅቱ ተደራሽ ለማድረግ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን የግብርና ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡
በአማራ ክልል የ2016/17 ምርት ዘመን የአፈር ማዳበሪያ አቅርቦት እና ሥርጭት ጉዳዮች ላይ የፌዴራል እና የክልል የሥራ ሃላፊዎች እንዲሁም ባለድርሻ አካላት በተገኙበት ውይይት ተካሂዷል፡፡
የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ በዚህ ወቅት እንዳሉት÷ለአርሶ አደሩ የአፈር ማዳበሪያ እና ሌሎች ግብዓቶችን በወቅቱ ተደራሽ ማድረግ ይገባል፡፡
የመድረኩ ዓላማም በቀጣይ የሥራ አቅጣጫዎች ዙሪያ የጋራ መግባባት ላይ ለመድረስ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
የግብርና ሚኒስትር ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) በበኩላቸው÷ የ2016/17 ምርት ዘመን የአፈር ማዳበሪያን በወቅቱ ለአርሶ አደሩ ለማድረስ በርካታ ሥራዎች እየተሰሩ መሆኑን አብራርተዋል፡፡
የትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ ሚኒስትር ዓለሙ ስሜ (ዶ/ር)÷ የአፈር ማዳበሪያ ግዢ ተፈፅሞ በአግባቡ ተጓጉዞ በወቅቱ ከአርሶ አደሩ እንዲደርስ በትኩረት እየተሰራ ነው ማለታቸውን የሚኒስቴሩ መረጃ ያመላክታል፡፡
የአማራ ክልል የ2016/17 ምርት ዘመን የአፈር ማዳበሪያ አቅርቦት እና ስርጭት የአፈፃፀም ሪፖርት ያቀረቡት ደግሞ በግብርና ሚኒስቴር የኢንቨስትመንትና ግብይት ዘርፍ ሚኒስትር ዴዔታ ሶፊያ ካሳ (ዶ/ር) ናቸው፡፡
በሪፖርታቸውም የአፈር ማዳበሪያ ግዢ ላይ የተደረጉ ማሻሻያዎች፣ የምርት ዘመኑ የማዳበሪያ አቅርቦት ያለበት ደረጃ፣ በአቅርቦት ሂደት ያጋጠሙ ተግዳሮቶችና መፍትሄ የሚሹ ጉዳዮችን አመላክተዋል፡፡