አዲስ አበባ፣ ጥር 15፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) 65 ዩክሬናውያን የጦር እስረኞችን ይዟል የተባለ የሩሲያ አውሮፕላን መከስከሱ ተሰምቷል፡፡
ንብረትነቱ የሩሲያ የሆነው ወታደራዊ አውሮፕላን ሀገሪቱ ከዩክሬን በምትዋሰንበት ደቡባዊ ቤልጎሮድ ግዛት ነው የተከሰከሰው፡፡
የሩሲያ መከላከያ ሚኒስቴር እንዳስታወቀው÷ አውሮፕላኑ 65 የዩኩሬን ጦር እስረኞችን በመያዝ ለእስረኞች ልውውጥ ወደ ቤልጎሮድ ግዛት አያመራ ነበር።
በአውሮፕላኑ ውስጥ ስድስት የአውሮፕላኑ ሰራተኞችን ጨምሮ ሌሎች ዘጠኝ ሰዎች እንደነበሩ ሪያ ኖቮስቲ የዜና ወኪል አስታውቋል።
በአውሮፕላኑ ውስጥ የነበሩት ሁሉም ሰዎች ሕይወት ማለፉንም በሩሲያ የቤልጎሮድ ግዛት አስተዳደር ቭያቼስላቭ ግላድኮቭ ተናግረዋል።
ዩክሬን በበኩሏ÷አውሮፕላኑ ለሩሲያ ኤስ-300 የተሰኙ የአየር መከላከያ ሚሳኤሎችን እያጓጓዘ ነበር ማለቷን ቢቢሲ በዘገባው ጠቁሟል፡፡
የአደጋው መንስኤ እና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ምርመራ መካሄድ መጀመሩም ተመላክቷል፡፡