የሀገር ውስጥ ዜና

ኢትዮጵያና ጣሊያን በስራ እድል ፈጠራ በጋራ ለመስራት ተፈራረሙ

By Amele Demsew

January 24, 2024

አዲስ አበባ፣ ጥር 15፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ መንግስት እና የጣሊያን መንግስት በስራ እድል ፈጠራ ተኮር ክህሎትና የመሰረተ ልማት ዝርጋታዎችን ለመደገፍ የትግበራ ስምምነት ተፈራርመዋል፡፡

በስምምነቱም ፥ ጣሊያን በድምሩ 12 ሚሊየን ዩሮ (748 ሚሊየን ብር) ፥ ማለትም 10 ሚሊየን ዩሮ ብድር እና 2 ሚሊየን ዩሮ የገንዘብ ድጋፍ ለማድረግ ተስማምተዋል፡፡

ፕሮጀክቱ ከጣሊያን የዘርፉ ባለሙያዎች ጋር የልምድ ልውውጥ በማድረግና የዘርፉን ክህሎት በማዳበር በተለይም ሴቶችና ወጣቶችን ያሳተፈ የስራ እድልና የገበያ ትስስር ለመፍጠር ታሳቢ ያደረገ ነው ተብሏል፡፡

የትግበራ ስምምነቱ በየዓመቱ ወደ 2 ሚሊየን የሚጠጉ አዳዲስ ስራ ፈላጊ ወጣቶች የስራ እድል ለመፍጠር ለሚደረገውሀገራዊ እንቅስቃሴ አስተዋጽኦ እንደሚያደርግ መገለጹን ከገንዘብ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

የትግበራ ስምምነቱን የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታዋ ሰመሪታ ሰዋሰው እና በኢትዮጵያ የጣሊያን አምባሳደር የሆኑት አጎስቲኖ ፓሌዝ ተፈራርመዋል፡፡