Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

በማህበራዊ ሚዲያ የሚላኩልን አሳሳች አጓጊ መልዕክቶችና መከላከያ መንገዶቹ

አዲስ አበባ፣ ጥር 14፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ)በአሁኑ ወቅት የሳይበር ጠላፊዎች የማህበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎችን ገጽ ለመንጠቅ የተለያዩ አማራጮችን እየተጠቀሙ እንደሆነ ይታወቃል፡፡

ከእነዚህ አማራጮች ውስጥም የፌስቡክ አጓጊ ወይም የማስገር (Phisining attack) የሚባለው ይገኝበታል፡፡

“እኔ አላምንም ! ሄደ! በጣም ይናፍቀኛል! (“I can’t believe he is gone. I’m gonna miss him so much) በመሳሰሉ አጓጊ የጽሑፍ መልክቶች የፌስቡክ የማስገር ዘመቻ (Phisining attack) እየተሰራጨ እንደሚገኝ ተመላክቷል፡፡

ተጠቃሚዎች በጽሑፍ መልዕክቱ አጓጊነት ተታለው ሊንኩን ሲጫኑት የፌስቡክ የይለፍ ቃሎቻቸው በሳይበር ጠላፊዎች እጅ ይወድቃል፡፡

እነዚህ የፌስቡክ ማስገሪያ (Phisinning) መልዕክቶች በሁለት መልኩ የሚሰራጩ ሲሆን ፥ አንደኛው አጓጊ የጽሑፍ መልዕክትና ከጎኑ ወደ አጭበርባሪዎቹ ገጽ የሚወስደው ሊንክ እንደሚኖረውም ነው የተገለፀው፡፡

ሁለተኛው ደግሞ ተመሳሳይ ጽሑፍ ይጠቀምና ከታዋቂ የቴሌቪዥን ጣቢያ የተቀዳ የሚመስል የመኪና አደጋ ወይም ሌላ የወንጀል ትዕይንት የሚያሳይ አሳሳች ተንቀሳቃሽ ምስል ከጎኑ ይቀመጥለታል፡፡

እንደሚጠቀሙት የዲቫይስ ዓይነት ቢለያይም ሊንኩን ሲጫኑት በደንብ የማይታይ ምስል ይመጣና ሙሉውን ቪዲዮ ለማየት የፌስቡክ የማንነት እና የይለፍ ቃል እንዲያስገቡ በመጠይቅ ወደ ሌላ ገጽ ይመራዎታል፡፡

አጭበርባሪዎቹ የይለፍ ቃልዎን ሰርቀው በእርስዎ አካውንት ለሌሎች ጓደኞችዎ በመላክ የማያቋርጥ የማስገር ማጭበርበርን ይፈጽማሉ፡፡

የማስገር ዘመቻው የጀመረው ከአንድ ዓመት በፊት ሲሆን ፥ የፌስቡክ ካምፓኒ እስከ ዛሬ ድረስ ልጥፎቹን ለማገድ አዳጋች ሆኖበታል ተብሏል።

ይሁንና አዳዲስ የማስገሪያ መልዕክቶች እንደተፈጠሩ ለፌስቡክ ሪፖርት ካደረጉ ፤ ፌስቡክ ወደ አጭበርባሪዎቹ ድረ-ገጽ የሚያመራውን ሊንክ እንዳይሰራ ማድረግ ይችላል፤ይህን በማድረግ በርካቶችን ከጥቃት መታደግም ይችላሉ፡፡

ታዲያ ይህን ዓይነት የማስገር ጥቃት እንዴት መከላከል ይቻላል?

ባለሁለት ደረጃ ማረጋገጫ (two-factor authentication) የይለፍ ቃል መጠቀም ከዚህ ዓይነት ጥቃት ይታደጋል።

ይህን የይለፍ ቃል ከተጠቀሙ ወደ አካውንትዎ ካልተለመደ ቦታ እና ዲቫይስ ለመግባት የሚሞክር አካል ሲኖር ፌስቡክ ወደ ተለመደው ዲቫይስ ለየት ያለ የአንድ ጊዜ የይለፍ ኮድ ይልክልዎታል፡፡

ይህ ኮድ ወደ እርስዎ ዲቫይስ ብቻ ስለሚመጣ አጭበርባሪዎቹ አያገኙትም ወደ አካውንትዎም መግባት አይችሉም ማለት ነው፡፡

ባለ ሁለት ደረጃ ማረጋገጫ ከተጠቀሙ ስልክዎ ቢሰረቅ እንኳን ሲምዎን በማዘጋት ተቀያሪ ሲም በወሰዱ ጊዜ የይለፍ ቃልዎን እንደገና ለማስተካከል ስለሚችሉ ከጥቃት ይድናሉ ሲል መረጃውን የኢንፎርሚሽን መረብ ደህንነት አጋርቷል፡፡

Exit mobile version