Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

የወርቅ ምርቱ በሚፈለገው ልክ እንዳያድግ ኮንትሮባንድ ተግዳሮት ሆኗል ተባለ

አዲስ አበባ፣ ጥር 14፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የጋምቤላ ክልል ማዕድን ሐብት ልማት ቢሮ የኮንትሮባንድ መበራከት ወደ ብሔራዊ ባንክ እንዲገባ በሚጠበቀው የወርቅ ምርት መጠን ላይ ዋነኛ ተግዳሮት ሆኖብኛል አለ፡፡

በተያዘው በጀት ዓመት የመጀመሪያ አጋማሽ 625 ኪሎ ግራም የወርቅ ምርት ለማግኘት ታቅዶ ወደ ሥራ ቢገባም የተገኘው ምርት 154 ነጥብ 29 ኪሎ ግራም ብቻ መሆኑን የቢሮው ኃላፊ አኳታ ቻም ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ገልጸዋል፡፡

ባለፈው በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወቅት 81 ነጥብ 052 ኪሎ ግራም ወርቅ ወደ ብሔራዊ ባንክ መግባቱን አስታውሰው÷ የዘንድሮ አፈጻጸም ካለፈው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር 73 ነጥብ 2 በመቶ ብልጫ አሳይቷል ብለዋል፡፡

ምንም እንኳን አፈጻጸሙ ካለፈው ወቅት አንጻር የተሻለ ቢሆንም በክልሉ እንዲመረት እና ወደ ብሔራዊ ባንክ እንዲገባ የሚጠበቀውን ወርቅ በማምረት ሂደት የኮንትሮባንድ መበራከት አሁንም ዋነኛ ችግር መሆኑን በአጽንኦት ገልጸዋል፡፡

ኮንትሮባንድን ለመከላከልም ወርቅ አምራች በሆኑ ሁለት ዞኖች እና አራት ወረዳዎች ኮማንድ ፖስቱ ክትትልና ቁጥጥር እያደረገ መሆኑን ገልጸው÷ ከዞን፣ ወረዳዎች ቀበሌዎች እና ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡

በ2016 የበጀት ዓመትም 1 ሺህ 250 ኪሎ ግራም የወርቅ ምርት ወደ ብሔራዊ ባንክ ለማስገባት መታቀዱን አመላክተዋል፡፡

በዮሐንስ ደርበው

Exit mobile version