Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

ዓለም አቀፍ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ዲፕሎማሲ አማካሪ ፎረም ተቋቋመ

አዲስ አበባ ፣ ጥር 13 ፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ዓለም አቀፍ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ዲፕሎማሲ አማካሪ ፎረም በዛሬው ዕለት ተቋቁሟል፡፡

ኢትዮጵያ ዳያስፖራውን በማሳተፍ ሒደት የገጠሟት ፈተናዎች ፣የተገኙ ውጤቶችና ቀጣይ ሥራዎች ላይ ትኩረት ያደረገ የፓናል ውይይት በሳይንስ ሙዚዬም ተካሂዷል፡፡

በዚሁ ጊዜም ዓለም አቀፍ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ዲፕሎማሲ አማካሪ ፎረም የተቋቋመ ሲሆን÷ ፎረሙ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በሀገር ልማት ላይ የበለጠ እንዲሳተፉ ለማድረግ ያለመ ነው፡፡

ፎረሙ ዳያስፖራው ምን ይፈልጋል፤ የዳያስፖራ ጥቅም ከማስከበር አኳያ ምን አይነት ስራዎች ሊከናወኑ ይገባል የሚለውን ከመንግሥት ጋር በመነጋር የሚሰራ ይሆናል ተብሏል፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደዔታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ በዚሁ ጊዜ እንዳሉት÷ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በተለያዩ የልማት መስኮች አበረታች ተሳትፎ እያደረጉ ነው፡፡

ይሄን ተሳትፎ ከፍ ወዳለ ደረጃ ማሸጋገር እንደሚገባ ጠቁመው÷ መንግሥት ዳያስፖራ አባላት ተሳተፎ ማሳደግ ላይ ትኩረት ማድረጉን መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

በኢትዮጵያ ያሉ ችግሮች የሚፈቱት በጋራ ትብብር መሆኑን ጠቅሰው÷ ሀገር ግንባታ ላይ ምሁራን፣በውጭ የሚኖሩ ዳያስፖራ አባላት ከመንግሥት ጋር የበለጠ በመቀራረብ ሚናቸውን እንዲወጡም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

Exit mobile version