ዓለምአቀፋዊ ዜና

ኔታንያሁ ሃማስ የታገቱ እስራኤላውያንን ለመልቀቅ ያቀረበውን ሃሳብ ውድቅ አደረጉ

By Melaku Gedif

January 22, 2024

አዲስ አበባ፣ ጥር 13፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ የጋዛ ጦርነት እዲያበቃና የታገቱ እስራኤላውያንን ለመልቀቅ ሃማስ ያቀረበውን ሃሳብ ውድቅ አድርገዋል፡፡

ሃማስ ከእስራኤል ጋር እያካሄደ ያለውን ደም አፋሻስ ጦርነት ማስቆም ያስችላል ያለውን ሃሳብ ይፋ ማድረጉ ይታወሳል፡፡

በዚህም እስራኤል በጋዛ እያካሄደች ያለውን ወታደራዊ ዘመቻ ካቆመች እና ጦሯን ካስወጣች የታገቱ እስራኤላውያንን እንደሚለቅ ሃማስ አስታውቋል፡፡

ጉዳዩን አስመልክተው ጠቅላይ ሚኒስትር ኔታንያሁ በሰጡት መግለጫ÷ ሃማስ በጋዛ እየተካሄደ ያለው ጦርነት እዲያበቃ በሚል ያቀረበው ሃሳብ ፍጹም ተቀባይት እንደሌለው ተናግረዋል፡፡

ሃሳቡን መቀበል መስዋዕትነት በከፈሉ የእስራኤል ወታደሮች ላይ እንደመቀለድ ይቆጠራል ነው ያሉት ኔታንያሁ፡፡

ሃማስ ሽንፈትን እየተጎነጨ እንደሚገኝ የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ÷ ቡድኑ ጦርነቱን ማስቆም ያስችላል በሚል ያቀረበውን ሃሳብም ውድቅ አድርገዋል፡፡

በሁሉም ግንባር የተጀመረው ጦርነት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠው÷ ለየትኛውም ሽብር ቡድን የመውጫ በር እንደማይሰጡ አስገንዝበዋል፡፡

እንደ እስራኤል ባለሥልጣናት መረጃ÷ እስካሁን 136 እስራኤላውያን በሃማስ ታግተው ይገኛሉ፡፡

የታጋች ቤተሰቦች እና ሌሎች አካላትም ታጋቾችን በድርድር ማስለቀቅ ይገባል በሚል ጥያቄ እያቀረቡ መሆናቸውን አልጀዚራ ዘግቧል፡፡

እስራኤል በጋዛ ላይ እየወሰደችው ባለው ወታደራዊ እርምጃ እስካሁን ሴቶች እና ሕጻናትን ጨምሮ ከ25 ሺህ በላይ ዜጎች ሕይወት ማለፉን መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡

በሌላ በኩል በትናንትናው ዕለት የሰብዓዊ እርዳታ የጫኑ 260 ተሽከርካሪዎች ወደ ጋዛ መግባታቸው ተገልጿል፡፡