Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥ ጉባዔ ውሳኔዎችን ለመተግበር ቁርጠኛ መሆኗን ገለጸች

 

አዲስ አበባ፣ ጥር 13፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ የ28ኛው የአየር ንብረት ለውጥ ጉባዔ ውሳኔዎችን ለመተግበር ከሁሉም አጋር አካላት ጋር በትብብር ለመስራት ቁርጠኛ መሆኗን የፕላንና ልማት ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

ሚኒስቴሩ በተባበሩት ዓረብ ኤሚሬቶች አዘጋጅነት በዱባይ ከተማ በፈረንጆቹ ካሳለፍነው ሕዳር 30 እስከ ታህሳስ 12 ቀን ድረስ የተካሄደውን 28ኛው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባዔ አስመልክቶ ማብራሪያ ሰጥቷል፡፡

በማብራሪያውም÷ኢትዮጵያ በተመድ የአየር ንብረት ለውጥ ጉባዔ (COP28) በዝርዝር በተካሄዱ የአየር ንብረት ለውጥ ድርድሮች እንዲሁም ኢትዮጵያ እያከናወነቻቸው ባሉ የአየር ንብረት ለውጥ ምላሽ ፕሮጀክቶች ተያያዥ ጉዳዮች ስኬታማ ተሳትፎ አድርጋ መመለሷን አስታውሷል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተሳተፉበት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባዔ ላይ ባደረጉት ንግግር÷በአየር ንብረት ለውጥ የተነሳ ሀገሪቷን እየገጠሙ ለሚገኙ ችግሮች ምላሽ ለመስጠት በአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ከ32 ነጥብ 5 ቢሊየን በላይ ችግኞች መተከላቸውን እንዳሳወቁም ጠቅሷል፡፡

በስንዴ ምርት፣በታዳሽ ኃይል አቅርቦት፣ በምግብ ራስን ለመቻል የተወጠነው የሌማት ትሩፋት እንዲሁም የትራንስፖርት ዘርፍ ለአየር ንብረት ለውጥ ተስማሚ አማራጭ የትራንስፖርት ዘርፎች ማበረታቻ የተወሰዱ እርምጃዎችን በዝርዝር እንዳስረዱም ሚኒስቴሩ አስረድቷል፡፡

ኢትዮጵያ የምትወስዳቸው የአየር ንብረት ለውጥ እርምጃዎች በእዳ መቆለል የተነሳ ከፍተኛ ተግዳሮት እየገጠማቸው መሆኑን ጠቅሰው÷የሚመለከታቸው ሀገራትና ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ተገቢ ማሻሻያ እንዲያርጉ መጠየቃቸውንም መግለጫው አስታውሷል፡፡

እንዲሁም የአየር ንብረት ተጽዕኖ ተጋጭነትን በትብብር ስለመፍታት፣ ፍትሃዊ፣ ተመጣጣኝ፣ ተደራሽ እና ስርዓት ያለው የኢነርጂ ሽግግር እና የቡድን 77 እና ቻይና ጉባኤ በሚመለከታቸው የዘርፉ ሚኒስትሮች ጋር ኢትዮጵያ ተሳትፎ ማድረጓ ተጠቁሟል፡፡

በዚህም ሁሉን ተጠቃሚ ሊያደርጉ በሚችሉ ጉዳዮች ላይ የኢትዮጵያን አቋምና ሀሳብ ማጋራት እንደተቻለ ነው የተገለጸው፡፡

በጉባዔው ወቅት ኢትዮጵያ “ዩ ኤ ኢ ዔ ኤም ኢ ዔ ፖወር” ከተሰኘ ድርጅት ጋር የ600 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር የ300 ሜጋ ዋት የንፋስ ኃይል ማንጫ ፕሮጀክትእንዲሁም ከጣሊያን የ8 ሚሊየን ዩሮ የአካባቢ ልማት እና የአየር ንብረት ለውጥ ሥራዎችን በትብብር ለመስራት ስምምነት መፈራረሟ ተመላክቷል፡፡

በ28ኛው የተመድ የአየር ንብረት ለውጥ ጉባዔ ኢትዮጵያ በመሪነት እንደተሳተፈች የገለጸው ሚኒስቴሩ÷አባል በሆነችባቸው የአፍሪካ ቡድን፣ በዝቅተኛ የእድገት ደረጃ የሚገኙ ሀገራት ቡድን በመምራትም መሳተፏን አስታውቋል፡፡

በተለይ የወቅቱ የአፍሪካ የአካባቢ ሚኒስትሮች ጉባዔ ፕሬዚዳንት እንደመሆኗ በጉባዔውአፍሪካውያን በአንድ ድምጽ እንዲደራደሩና ጥቅማቸውን እንዲያስጠብቁ አስተባብራለች ተብሏል፡፡

በጉባዔው ወቅት የበለጸጉ ሀገራት ለታዳጊ ሀገራት ለአየር ንብረት ለውጥ ምላሽ የሚውል የ792 ሚሊየን የአሜሪካን ዶላር የአየር ንብረት ለውጥ የሚያስከትለውን ጥፋትና ውድመት ፈንድን ጨምሮ የ85 ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር ለመስጠትም ቃል እንደገቡ ተጠቁሟል፡፡

የዓለም ባንክ በበኩሉ ከአየር ንብረት ለውጥ ተያያዥ ለሆኑ ፕሮጀክቶች በ2024 እና 2025 የ9 ቢሊየን የአሜሪካን ዶላር ጭማሪ ማድረጉ ተገልጿል፡፡

እንዲሁም የባለብዙ ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት ለአየር ንብረት ለውጥ ምላሽ ድጋፎች ከ22 ነጥብ 6 ቢሊየን የአሜሪካን ዶላር ተጨማሪ በጀት ለመመደብ ቃል ገብተዋል ነው የተባለው፡፡

በኢትዮጵያ በተለያየ ዘርፍ ያሉትን ራዕዮችና አሁን እየተከናወኑ ያሉ ተግባሮችን በኢትዮጵያ አረንጓዴ አሻራ ፓቪሎን በኤግዝቢሽን መልኩ እንደቀረቡ ተገልጿል፡፡

ኢትዮጵያ በተመድ ማዕቀፍ በባለብዙ የትብብር ማዕቀፎች ያላትን እምነት መሰረት በማድረግ የ28ኛው የአየር ንብረት ለውጥ ጉባዔ ውሳኔዎችን ለመተግበር እና በትግበራ ሂደት ከሁሉም አጋር አካላት ጋር በትብብር ለመስራት ቁርጠኛ መሆኑንም ሚኒስቴሩ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት በላከው መረጃ አስታውቋል፡፡

Exit mobile version