አዲስ አበባ፣ ጥር 13፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ የዱር እንስሣት ጥበቃ ባለስልጣን ብሔራዊ ፓርኮች ለዱር እንስሣት እና ለጎብኚዎች እንዲመቹ እየሠራሁ ነው አለ፡፡
በዱር እንስሣት ጥበቃ ቦታዎች ከ108 ኪሎ ሜትር በላይ የውስጥ ለውስጥ መንገድ መጠገኑ እና በማዜ ብሔራዊ ፓርክም የሬንጀሮች መኖሪያ ቤት ለአገልግሎት ዝግጁ መሆኑ ተነስቷል፡፡
በስሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክም ድብ ባሕር፣ ሊማሊሞ፣ ኬላ፣ ሳንቃ በር፣ ጨነቅ፣ ጠቅላይ ሠፈር፣ ትልቱና ሰባት ምንጭ የሬንጀሮች መኖሪያ ቤቶች ተጠግነው አገልግሎት እንዲሰጡ መደረጉ ተገልጿል፡፡
የያንጉዲራሳ ብሔራዊ ፓርክ ጽሕፈት ቤት ግንባታም ከ67 በመቶ በላይ መድረሱን የባለስልጣኑ የኮሙኒኬሽን ባለሙያ ናቃቸው ብርሌው ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት አስታውቀዋል፡፡
በጥበቃ ቦታዎች ዙሪያ ለ51 ሺህ 379 የቤት እንስሣት ክትባት መሠጠቱን ጠቅሰው÷ የመድኃኒት መግዣ በጀት እጥረት ሥራው በሚጠበቀው ልክ እንዳሄይድ አድርጎታል ብለዋል፡፡
74 ሺህ 600 ጎብኚዎች ፓርኮቹን መጎብኘታቸውን አንስተው÷ ከዱር እንስሣት ፍጆታዊ እና ኢ-ፍጆታዊ አጠቃቀምም 64 ነጥብ 45 ሚሊየን ብር ገቢ መገኘቱን ጠቅሰዋል፡፡
በጥበቃ ቦታዎች የሚካሄዱ ሕገ-ወጥ ድርጊቶችን 66 በመቶ መቀነስ መቻሉንም ተናግረዋል፡፡
እንዲሁም በባሌ ተራራዎች ብሔራዊ ፓርክ ዙሪያ ሕገ-ወጥ እንቅስቃሴ መቀነሱን ያመላከቱት ባለሙያው በሀረና ደንና ሰነቴ ልቅ ግጦሽ 97 በመቶ መቀነሱን አረጋግጠዋል፡፡
በዮሐንስ ደርበው