አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 24 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) ባለፉት 24 ሰዓታት ለ2 ሺህ 926 ሰዎች የላቦራቶሪ ምርመራ ተደርጎ 85 ሰዎች የኮሮና ቫይረስ እንደተገኘባቸው የጤና ሚኒስቴር አስታወቀ።
ይህን ተከትሎም በአጠቃላይ በሀገራችን ቫይረሱ በምርመራ የተገኘባቸው ሰዎች ቁጥር 1 ሺህ 257 ደርሷል።
ቫይረሱ የተገኘባቸው እድሜያቸው ከ1 ወር እስከ 65 አመት የሚገኙ ሲሆን፥ 51 ወንድ እና 34 ሴቶች ናቸው ተብሏል።
ከዚህ ውስጥ 72 በአዲስ አበባ፣ 4 ሰዎች ትግራይ ክልል፣ 5 ሰዎች ኦሮሚያ፣ 1 ሰው አማራ ክልል እንዲሁም 3 ሰዎች ሶማሌ ክልል ናቸው።
19ኙ የውጭ ሃገር የጉዞ ታሪክ ያላቸው ሲሆን፥ 18 ሰዎች ደግሞ በቫይረሱ ከተያዘ ሰው ጋር ግንኙነት ያላቸው እንዲሁም 48 ሰዎች በቫይረሱ ከተያዘ ሰው ጋር ግንኙነትም ሆነ የውጭ ሃገር የጉዞ ታሪክ የሌላቸው መሆኑ ታውቋል።
የኮሮና ቫይረስ በምርመራ ተገኝቶበት በኤካ ኮተቤ ህክምና ሲደርግለት የነበረና ከዚህ ቀደም ተጓዳኝ ህመም ያለበት የ30 ዓመት ኢትዮጵያዊ በትናንትናው ዕለት ህይወቱ አልፏል።
ይህን ተከትሎም በአጠቃላይ በሀገራችን ቫይረሱ ተገኝቶባቸው ህይወታቸው ያለፈ ሰዎች ቁጥር 12 ደርሷል።
በሌላ መልኩ በትናንትናው ዕለት 8 ሰዎች (ሶስት ከኦሮሚያ ክልል እና አምስት ከአዲስ አበባ) ያገገሙ ሲሆን በአጠቃላይ በሀገራችን ከቫይረሱ ያገገሙ ሰዎች ቁጥር 217 ሆኗል።