የሀገር ውስጥ ዜና

የኢትዮጵያ አየር ኃይል በርካታ የአፍሪካ ሀገራት ለእውቀት ሽግግር ድጋፍ የሚጠይቁት ተቋም ሆኗል – ሌ/ጄ ይልማ መርዳሳ

By Melaku Gedif

January 20, 2024

አዲስ አበባ፣ ጥር 11፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ አየር ኃይል በበርካታ አፍሪካዊያን ሀገራት ለእውቀት ሽግግር ድጋፍ የሚጠየቅ ተመራጭ ተቋም ለመሆን መብቃቱን የኢትዮጵያ አየር ኃይል አዛዥ ሌተናል ጄኔራል ይልማ መርዳሳ ገለጹ።

ሌ/ ጄ ይልማ መርዳሳ በወቅታዊ የተቋሙ ተልዕኮና የሥራ አፈፃፀም ዙሪያ ከአየር ኃይል ክፍሎች ከተውጣጡ የሰራዊቱ አመራሮች ጋር ተወያይተዋል።

በዚሁ ወቀት ሌ/ጄ ይልማ መርዳሳ÷የኢትዮጵያ አየር ኃይል በአሁን ወቅት መልቲ ሮል ፋይተር የሆነው su 30 ተዋጊ ጄት እስከ ስትራቴጂክ የሰው አልባ አውሮፕላን ድረስ መታጠቁን አምስተዋል፡፡

በተጨማሪም በሌሎች የአቭዬሽን መመዘኛዎች ፕሮፌሽናሊዝምን በከፍተኛ ደረጃ ማሳደግ መቻሉን ነው የገለጹት፡፡

ይህን መልካም ገፅታውን የተረዱ በርካታ አፍሪካዊያን ሀገራት ለእውቀት ሽግግር ድጋፍ የሚጠይቁት ተመራጭ ተቋም ለመሆን በቅቷል ብለዋል።

“የሃያላን ሀገራት ፉክክርና የታዳጊ ሀገሮች ፈተና የበዛበት እንዲሁም የአከባቢያችን ጂኦ ፖለቲካ ግጭት ካልራቀው የአፍሪካ ቀንድ ችግር ጋር ነገሮች ውስብስብ እየሆኑ መጥተዋል” ሲሉም ጠቅሰዋል፡፡

ሌ/ጄ ይልማ መርዳሳ አመራሮችም ይህን ዓለም አቀፋዊ ቀጣናዊ ብሎም ሀገራዊ ሁኔታን ከግምት ያስገባ የሰራዊት ሥነ ልቦና ግንባታ ላይ ትኩረት በማድረግ የወትሮ ዝግጁነት አቅም በማረጋገጥ ኃላፊነታቸውን ሊወጡ እንደሚገባ አሳስበዋል።

የሰራዊቱ አመራሮች ከውይይቱ መጠናቀቅ በኋላ ተቋሙ በቅርቡ የታጠቃቸውን የsu 30 ዘመናዊ የውጊያ ጄት አውሮፕላኖችንና ስትራቴጂክ የሰው አልባ አውሮፕላን ቴክኖሎጂን ተዘዋውረው መመልከታቸውን ከመከላከያ ሰራዊት ማህበራዊ ትስስር ገጽ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።