የሀገር ውስጥ ዜና

የቀድሞ የአ/አ ከተማ ከንቲባ የፕሮቶኮል ዳይሬክተር እነ ኤልቤቴል ሀብቴ በተጠረጠሩበት የሙስና ወንጀል 10 ቀናት የምርመራ ማጣሪያ ጊዜ ተፈቀደ

By ዮሐንስ ደርበው

January 19, 2024

አዲስ አበባ፣ ጥር 10፣2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የፌደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ ጊዜ ቀጠሮ ችሎት የቀድሞ የአ/አ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ የፕሮቶኮል ዳይሬክተር እነ ኤልቤቴል ሀብቴ በተጠረጠሩበት የሙስና ወንጀል 10 ቀናት የምርመራ ማጣሪያ ጊዜ ፈቀደ።

ተጠርጣሪዎቹ የቀድሞ የአ/አ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ የፕሮቶኮል ዳይሬክተር ኤልቤቴል ሀብቴ እና የፍትህ ሚኒስቴር ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ዘርፍ ሀብት አስተዳደር ዳይሬክተር ፍቅሩ ኦላና እንዲሁም በግል ስራ ይተዳደራሉ የተባሉት ቅዱስ መስፍን፣ አማኑኤል መስፍንና ተክሌ ከቡ የተባሉ ግለሰቦች ናቸው።

ችሎቱ ከዚህ በፊት በሰጠው የ14 ቀናት የምርመራ ጊዜ ውስጥ በፖሊስ የተሰሩ የምርመራ ውጤቶችን ተመልክቷል።

የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን መርማሪ ከዚህ በፊት በተሰጠው 14 ቀናት ውስጥ በርካታ ማስረጃዎችን ማሰባሰቡን፣ በተጠርጣሪዎቹ ስም የተንቀሳቀሱ ከፍተኛ መጠን ያለው የገንዘብ እንቅስቃሴን የሚያሳይ የባንክ ስቴትመንት ማቅረቡን፣ የአራት የሰው ምስክርና የተጠርጣሪዎችን ቃል መቀበሉን አብራርቷል።

በተጨማሪም የዋጋ ግምቱ 2 ሚሊዮን 500 ሺህ የሆነ የሰሌዳ ቁጥሩ ኮድ 2 (B) 81421 አ/አ የሆነ ተሽከርካሪን ለስራ ተገልግለን እንመልሳለን በሚል ምክንያት መወሰዱን የገለጸው መርማሪ ፖሊስ፤ የሞተርና የሻንሲ ቁጥርን በመለወጥ አዲስ በማስመሰል ሀሰተኛ ዲክላራሲዮን በማዘጋጀት የሰሌዳ ቁጥሩ ተቀይሮ ለሌላ ግለሰብ ተላልፎ መሸጡን የሚያመላክት አዲስ የምርመራ ግኝት መገኘቱን ገልጿል።

ከዚህ በተጨማሪማ ወንጀሉ የተፈጸመው በአንደኛ ተጠርጣሪ ስም ኬኬ የመኪና አስመጪ በሚል በተመሰረተ ድርጅት ስም መሆኑን ፖሊስ ጠቅሶ ይህን ድርጅት በሚመለከት ማስረጃ የማሰባሰብ ስራ እንደሚቀረው አብራርቷል።

በአጠቃላይ ወንጀሉ የተፈጸመው በቡድን መሆኑን የጠቀሰው መርማሪ ፖሊስ ተጨማሪ የምስክር ቃል ለመቀበልና ቀሪ የምርመራ ስራ ለማከናወን ጊዜ እንደሚያስፈልገው ገልጾ 14 ቀናት የምርመራ ጊዜ እንዲሰጠው ጠይቋል።

የተጠርጣሪ ጠበቆች በበኩላቸ የፖሊስ የጊዜ ቀጠሮ ምክንያቶች ተጠርጣሪዎችን በእስር ለማቆየት የሚያስችሉ አይደሉም በሚል የመከራከሪያ ነጥቦችን አንስተዋል።

ተሽከርካሪ ታርጋ ተቀይሮ ሀሰተኛ ዲክላራሲዮን ተዘጋጅቶ ለሌላ ግለሰብ ተሽጧል የተባው አዲስ ግኝትን በሚመለከት ማን ለማን ሸጠ የሚለውን ተለይቶ አልቀረበም በሚል ተከራክረዋል።

1ኛ፣ 2ኛ እና 5ኛ ተጠርጣሪዎችን በሚመለከት የ1ኛ ተጠርጣሪ ወንድም በህግ እንዳይጠየቅ ወደ ግል ተበዳዮች ስልክ በመደወል በቀነኒሳና ደሳለኝ ሆቴሎች ውስጥ ስብሰባ እየጠሩ ”አርፋችሁ ተቀመጡ ለዕቃ ማስመጫ ተብሎ ስለተወሰደው 47 ሚሊዮን 345 ሺህ ብር ጉዳይ እንዳታነሱ” እያሉ ያስፈራሯቸው ነበር በማለት ፖሊስ ያቀረበው ነጥብን በሚመለከት በተጠርጣሪ ጠበቆች በኩል ሆቴል የጠሯቸው ለማስፈራራት ሳይሆን ለሽምግልና ነው በሚል ተከራክረዋል።

በተጨማሪም የተጠርጣሪ ጠበቆች የፖሊስ የጊዜ ቀጠሮ መጠየቂያ ምክንያቶች ላይ የተጠርጣሪ ተሳትፎ ተለይቶ አልቀረበም በማለት የተከራከሩ ሲሆን የፖሊስ ጊዜ ቀጠሮ ጥያቄው ውድቅ እንዲደረግላቸው ጠይቀዋል።

ከዚህም ባሻገር ጠበቆቹ ከግል ተበዳዮች የተወሰደ ገንዘብን ለማስመለስ ነው በፖሊስ እየተሰራ ያለው የሚል ገለጻ ማቅረባቸውን ተከትሎ በፖሊስ በኩል መልስ ተሰጥቷል።

በዚህም መርማሪ ፖሊስ የግል ተበዳይን ገንዘብ የማስመለስ ስራ የኛ ሚና አይደለም በማለት ተጠርጣሪዎቹ በቡድን በመሆን የሙስናና የማታለል ወንጀል ፈጽመዋል በተባሉበት ጉዳይን በሚመለከት ተገቢውን የምርመራ ስራ እያከናወነ ማስረጃም እያሰባሰበ እንደሚገኝ አብራርቶ መልስ ሰጥቷል።

የግራ ቀኝ ክርክሩን እና የፖሊስን የጊዜ ቀጠሮ መዝገብ የመረመረው ችሎቱ ከወንጀሉ ውስብስብነት አንጻር ተጨማሪ የምርመራ ማጣሪያ ጊዜ ለፖሊስ መሰጠት እንዳለበት በማመን የተጠርጣሪዎችን የዋስትና ጥያቄ በማለፍ የምርመራ ማጣሪያ ጊዜ እንደሚያስፈልገው በማመን 10 ቀናት የምርመራ ማጠቃለያ ጊዜ ለፖሊስ ፈቅዷል።

በታሪክ አዱኛ