Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

ርዕሳነ-መስተዳድሮች እና ከንቲባዎች ለጥምቀት በዓል የመልካም ምኞት መግለጫ መልዕክት አስተላለፉ

አዲስ አበባ፣ ጥር 10፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የተለያዩ ክልሎች ርዕሳነ-መስተዳድሮች እና የከተማ አሥተዳደሮች ከንቲባዎች ለጥምቀት በዓል የመልካም ምኞት መግለጫ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ምክትል ርዕሰ መሥተዳድር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር ኢ/ር) ባስተላለፉት መልዕክት÷ የክርስትና ዕምነት ተከታዮች በዓሉን ሲያከብሩ በፍጹም የዕምነቱ አስተምኅሮ ሰላምን በመስበክ ሊሆን ይገባል ብለዋል።

በዓሉ ያለ ምንም የጸጥታ ችግር እንዲጠናቀቅም ምዕመናን እና ወጣቶች ከጸጥታ አካላት ጋር በመሆን የድርሻቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል።

በክልሉ የሚገኙ የክርስትና እምነት ተከታዮችም በዓሉን በችግር ውስጥ የሚገኙ ወገኖችን በመደገፍ፣ ላጡት በመለገስ፣ በፍቅርና በአብሮነት እንዲያከብሩ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጥላሁን ከበደ በበኩላቸው የከተራና ጥምቀት በዓላት ሃይማኖታዊ ሥርዓቱን ከባህላዊ ወግ ጋር አስተሳስረው የያዙ በብዙ ህብረ ቀለማት የታጀቡ ናቸው ብለዋል።

”በዓሉ ዕሴቱን ጠብቆ በማክበር አብሮነታችንና አንድነታችንን ይበልጥ እንዲደምቅ ማድረግ ይገባናል” ያሉት አቶ ጥላሁን በዓሉን በሰላምና በደስታ እንዲያሳልፉ አስፈላጊ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች መከናወናቸውን ገልጸዋል።

የአማራ ክልል ፕሬዚዳንት ፅህፈት ቤት የከተራ እና ጥምቀት በዓልን አስመልክቶ ባስተላለፈው መልዕክት ÷በዓሉን ስናከበር ሰላምን በማጽናት፣ በመጠበቅ እና በመንከባከብ ሊሆን ይገባል ብሏል፡፡

ለጋራ ሰላማችን መጽናት ሁሉም አካል የበኩሉን አስተዋጽኦ ሊያበረክት ይገባልም ነው ያለው።

በዓሉን ስናከብር በወንድማማችነት ስሜት የተቸገሩ ወገኖችን በማሰብ፣ በመፈቃቀድ በመተሳሰብና በመደጋገፍ በሰላም፣ በፍቅርና በደስታ እንዲሆንም መልዕክቱን አስተላልፏል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አሥተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ባስተላለፉት መልዕክት÷ ለጥምቀት ወደ ከተማችን የሚመጡ እንግዶችንም በኢትዮጵያዊ ጨዋነት ለማስተናገድ ተዘጋጅተናል ብለዋል፡፡

በዓሉን ስናከብርም በመተሳሰብ፣ አብሮነታችንን በማጠናከር፣ በፍቅር፣ በደስታና በሰላም ሊሆን ይገባል ብለዋል በመልዕክታቸው፡፡

የድሬዳዋ ከተማ አሥተዳደር ከንቲባ ከድር ጁሀር በበኩላቸው የጥምቀት በዓል ወንድማማችነትን እንደሚያጠናክር ጠቅሰው÷ በሀገር ግንባታ ሂደትም ትልቅ መሳሪያ ሆኖ እንደሚያገለግል ገልጸዋል፡፡

ኅብረተሰቡም በዓሉን ሲያከብር የመረዳዳት እና የመደጋገፍ ባሕሉን በማጠናከር ብሎም የአሥተዳደሩን ሰላም በማጠናከር መሆን ይገባዋል ብለዋል፡፡

Exit mobile version