ኢትዮ ቴሌኮምና ዜድቲኢ ኩባንያ የተለያዩ ተንቀሳቃሽ ስልኮችን በጋራ ለገበያ ለማቅረብ ተስማሙ
አዲስ አበባ፣ ጥር 9፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮ ቴሌኮም እና ዜድቲኢ ኩባንያ የ’ዜድቲኢ ብሌድ ቨርዥን 50’ ዲዛይንን ጨምሮ የተለያዩ ተንቀሳቃሽ ስልኮችን በጋራ ለገበያ ሊያቀርቡ መሆኑን አስታወቁ።
ኢትዮ ቴሌኮም የዜድቲኢ ብሌድ ቨርዥን V50 ዲዛይንን ጨምሮ A40 እና A54 ስማርት ስልኮችን ለደንበኞች ማቅረብ የሚያስችል ስምምነት ከዜድቲኢ ኩባንያ ጋር ተፈራርሟል።
የተደረሰው ስምምነትም ኢትዮ ቴሌኮምና ዜድቲኢ አዲስ ይፋ የሆነውን ዜድቲኢ ብሌድ V50 ዲዛይን ወደ ኢትዮጵያ ገበያ በጋራ ለማቅረብ የሚያስችል መሆኑ ተነግሯል።
ኢትዮ ቴሌኮም የስማርት ስልኮችን ተደራሽ ለማድረግ እና አጠቃላይ የዜጎችን የቴክኖሎጂ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ስማርት ስልኮችን በተመጣጣኝ ዋጋ በተለያዩ የመክፈያ ዘዴዎች ማቅረቡን የኢትዮ ቴሌኮም የቴክኖሎጂ ዘርፍ ዋና ሀላፊ ታሪኩ ደምሴ ተናግረዋል።
ኢትዮ ቴሌኮም በየአመቱ ከ1 ሚሊየን በላይ የተለያዩ ዓይነት ዲቫይዞችን ለተጠቃሚዎች ተደራሽ ለማድረግ ሲሰራ መቆየቱንም ጠቁመዋል።
በበረከት ተካልኝ