Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

በሐረር ከተማ የሃይማኖት አባቶች የጥምቀት በዓል ማክበሪያ ስፍራን አፀዱ

አዲስ አበባ፣ ጥር 9፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በሐረር ከተማ የሃይማኖት አባቶችና የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች የጥምቀት በዓል ማክበሪያ ስፍራን አፅድተዋል።

የሐረሪ ክልል የሰላምና የፀጥታ አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ አቶ ቶፊቅ መሃመድ ÷የጽዳት መርሐ ግብሩ ሐረር የምትታወቅበትን የአብሮነት፣ የፍቅርና የመቻቻል ዕሴትን የሚያንፀባርቅ ነው ብለዋል።

መሰል በጎ ተግባራት በሕዝቦች መካከል ያለውን አብሮነት የሚያጠናክሩ መሆናቸውንም አስገንዝበዋል፡፡

በዓሉ ተጀምሮ እስከሚጠናቀቅ ድረስ ያለውን ሰላም ጸጥታና ደህንነት ለማረጋገጥ ዝግጅት መደረጉን ገልፀው÷ ህብረተሰቡም ከፀጥታ ኃይሉ ጎን በመቆም ትብብር እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል።

የሃይማኖት አባቶች በበኩላቸው እንዳሉት÷መሰል መርሐ ግብር በእምነቱ ተከታዮች ዘንድ መከባበርን፣ ፍቅርን፣ ሰላምንና አንድነትን ከማጎልበት አንፃር ፋይዳው የላቀ ነው።

በተለይም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በክልሉ በሃይማኖት መካከል እየታየ የሚገኘው መደጋገፍ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ብለዋል።

በመርሐ ግብሩ ላይ የሃይማኖት አባቶች፣ የክልሉ የጸጥታ አባላትና አመራሮች፣ የወረዳ አመራሮች ፣ የተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎችና በጎ ፈቃደኞች መሳተፋቸውን የክልሉ ኮሙኒኬሽን መረጃ ያመላክታል፡፡

Exit mobile version