አዲስ አበባ፣ ጥር 9፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ከ30 በላይ ሀገራት ብሪክስን ለመቀላቀል ፍላጎት ማሳየታቸውን የሩሲያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡
የሩሲያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌይ ላቭሮቭ÷ የሀገሪቱን የ2023 ዓመታዊ የዲፕሎማሲ ክንውኖች አስመልክተው መግለጫ ሰጥተዋል፡፡
በመግለጫቸውም ÷ሩሲያ ከብሪክስ መስራች ሀገራት ጋር በመተባበር የብሪክስ አባል ሀገራትን ለማጠናከር ያደረገችው ጥረት የተሳካ እንደነበር ገልፀዋል፡፡
የብሪክስ አባል ሀገራትን ለማስፋት በተደረገው ጥረትም በ2023ቱ የብሪክስ ጉባዔ ኢትዮጵያን ጨምሮ ግብፅ፣ ኢራን እና የተባበሩት ዓረብ ኤሜሬቶችን የመሳሰሉ ሀገራት አባል መሆናቸውን ጠቅሰዋል፡፡
አሁን ላይ ብሪክስን ለመቀላቀል በርካታ ሀገራት ፍላጎት እንዳላቸው የገለፁት ሚኒስትሩ÷ከ30 በላይ የሚሆኑት የኢኮኖሚ ስብስብ የሆነውን ብሪክስ ለመቀላቀል ፍላጎት አሳይተዋል ብለዋል፡፡
ከእነዚህ ውስጥም ቬንዝዌላ፣ ታይላንድ፣ ሴኔጋል፣ ኩባ፣ ቤላሩስ፣ ባህሬን እና ፓኪስታን ብሪክስን ለመቀላቀል በይፋ ደብዳቤ ማስገባታቸውን ተናግረዋል፡፡
ሶሪያ፣ ቱርክ፣ ኒካራጓ፣ ኢንዶኔዥያ እና ዝምባቡዌ ደግሞ በግልጽ ማመልከቻ ባያስገቡም ብሪክስን ለመቀላቀል ፍላጎት ያሳዩ ሀገራት ናቸው መባሉን አር ቲ ዘግቧል፡፡